በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ ሴኔት የኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ ዕጩ አምባሣደሮችን ሹመት ፈተሸ


የኦባማ አስተዳደር ለአፍሪካ ያጫቸውን ከፍተኛ አምባሣደሮችን ሹመት ለማፅደቅ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ የማጣሪያ የምስክርነት ቃል ማድመጥ ጀምሯል።

አምባሣደር ፓትሪሽያ ኤም ሃስላክ
አምባሣደር ፓትሪሽያ ኤም ሃስላክ


please wait

No media source currently available

0:00 0:06:10 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

የኦባማ አስተዳደር ለአፍሪካ ያጫቸውን ከፍተኛ አምባሣደሮችን ሹመት ለማፅደቅ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ የማጣሪያ የምስክርነት ቃል ማድመጥ ጀምሯል።

ተሰናባቹን የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚተኩት ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ፣ ለኢትዮጵያ የተመደቡት አምባሣደር፣ እንዲሁም ሌሎች አራት አምባሣደሮች በሴኔቱ ፊት ቀርበው ሹመታቸው እንዲፀድቅ ጠይቀዋል።

ዛሬ - ረቡዕ፣ ሐምሌ 17/2005 ዓ.ም የተካሄደው በሴኔቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ክሪስ ኩንስ የተመራው የሹመት ማፅደቂያ ሰሚ ስብሰባ የኦባማ አስተዳደር ከፍተኛ የአፍሪካ ባለሥልጣን ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ፣ ለደቡብ አፍሪካ፣ ለኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ለናይጀሪያና ለአፍሪካ ህብረት ልትልካቸው ያሰበቻቸው ዕጩ አምባሣደሮች የተገኙበት ነው።

የኮንግረስ አባላቱ በአፍሪካ የፀጥታና ደኅንነት፣ የምጣኔ ኃብት ዕድገትና የግል ዘርፉ ሚና እንዲሁም ዴሞክራሲና የአገር አስተዳደር ጉዳዮችን አስመልክቶ ተሿሚዎቹ አምባሣደሮች የሚያስፈፅሟቸውን ፖሊሲዎች እንዲያስረዱ ጠይቀዋል።

በተለይ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ከለት ወደለት በፍጥነት እያደገ ዩናይትድ ስቴይትስን ካለፈቻት ዓመታት ተቆጥረዋል። የአሜሪካ የግል ዘርፍ በአፍሪካ መዋዕለ-ነዋይ እንዲያፈስስ በብቃት ሠርተናል ወይ? የአፍሪካን ጉዳይ ቸል የማለት ሁኔታ ይታያል ወይ? ሲሉ ሴናተር ኩንስ ወደ አምባሣደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ጥያቄ ሠንዝረዋል።

“አፍሪካን ቸል እያልን አይደለም። በግንኙነታችን ላይ ከፍተኛ አትኩሮት አለን። እውነት ነው ከዚህ በፊት የከፍተኛ ባለሥልጣናት የጋራ ጉባዔዎችን ለማሰናዳት አልቻልንም ነበር። አሁን ግንኙነቶቻችንን እያጠናከርን ነው፤ ለአፍሪካ ወሣኝ የልማትና የደኅንነት አጋርነታችን ይቀጥላ” ሲሉ መልሰዋል ሚስ ቴማስ-ግሪንፊልድ፡፡

ከእጩ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ቀጥሎ ለኢትዮጵያ የታጩት አምባሣደር ፓትሪሽያ ሀስላክ፣ የአፍሪካ ህብረቱ ልዑክ ሩብን ብሪጊሪ፣ ለናይጀሪያ የታሰቡት ጄምስ ኢንትዊስል፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ ስቴፈኒ ሱሊቫን እና የደቡብ አፍሪካው ዕጩ አምባሣደር ፓትሪክ ጋስፓርድ ይገኙባቸዋል።

በአምባሣደሮቹ የሹመት ሰሚ ስብሰባ ላይ የተገኙት ሦስት ሴናተሮች ሹመቱን እንደሚያፀድቁላቸው ነግረዋቸዋል። የቀረቡባቸው /በተለይ በግላቸው/ ትችቶችም የሉም። ሴናተሮቹ አብረናችሁ ልንሠራ ዝግጁ ነን ሲሏቸው ተሰምቷል። ነገር ግን ዋነኛ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረቶቻቸውን ለሴኔቱ እንዲያስረዱ ተጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴይትስ አምባሣደር እንዲሆኑ የታጩት ፓትሪሺያ ሃስላክ በ1977 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በድርቅ በተጠቃችበት ወቅት ህይወት አድን ሥራ ላይ ተሠማርተው የነበሩ፤ ቆይተውም የግብርና ምርትን ለማሣደግ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ልምድ ያላቸው ዲፕሎማት ናቸው።

በአዲስ አበባ ሹመታቸው ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ፖሊሲዎች አስረድተዋል።

“በአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ የአካባቢ ፀጥታና ደኅንነት ስልታዊ አጋራችን ናት። የአፍሪካ ኅብረት የፀረ-ሽብር መርኃግብሮችን በመምራት፣ በሶማሊያ ወታደሮቿን በማሠማራት፣ በሱዳን ደግሞ ድርድሮችን በማመቻቸት የሱዳንና ደቡብ ሱዳን መንግሥታት እንዲወያዩ በር ከፍተታለች። በነዚህ የጋራ ግቦቻን አብረን ሠርተናል፤ እንሠራለንም። ኢትዮጵያ ለስደተኞች በሮቿን የከፈተች አገር ናት። ሹመቴ ከፀደቀ፣ እነዚህ ግንኙነቶ እንዲጠናከሩ እሠራለሁ” ብለዋል፡፡

“በተጨማሪ የኢትዮጵያ ምጣኔኃብት በነፃነት የሚንቀሳቀስበትን መንገድም እንሻለን። ዕድገት፣ ልማትና ብልፅግና ከሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ከህግ የበላይነትና ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙና የማይነጠሉ እሴቶች እንደሆኑ ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳስባለሁ፤ አብሬያቸውም እሠራለሁ” ብለዋል ዕጩ አምባሣደር ሃስላክ፡፡
“ሹመቴ ከፀደቀ - አሉ ሃስላክ አክለው - ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር የፖለቲካ መድረኩ እንዲከፈት፣ የመናገር ነፃነቶች እንዲያብቡ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ፣ የመደራጀት መብቶችና የህግ-የበላይነት እንዲከበሩ እንሠራለን።”

አምባሣደር ሃስላክ አክለውም የፆታ ጥቃት፣ እንዲሁም የተመሳሳይ ፆታ ፍቅረኞች ላይ የሚደርሱ መገለልና ጥቃቶችን በፖሊሲ የመብቶች ይዞታዎች እንዲሻሻሉ እንደሚሠሩም ለሴኔቱ ተናግረዋል።
ሃስላክን ተከትለው በአምባሣደር ማዕረግ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙት በአፍሪካ ኅብረት የዩናይትድ ስቴትስ ቋሚ መልእክተኛ ሩብን ብርጊሪ ናቸው። በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የሠሩት ብርጊሪ የአፍሪካ ኅብረት የፖሊሲ ትኩረታቸውን ሲያስረዱ የትኩረት መስኮቻቸው
1ኛ. ዴሞክራሲና የሕዝብ አስተዳደር፣
2ኛ. የምጣኔኃብት ዕድገት፣ ንግድና መዋዕለ ነዋይ፣
3ኛ ሰላምና መረጋጋት፣
4ኛ የዜጎችን የተጠቃሚነት ዕድል ማስፋትና ልማት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪካ ከፍተኛ የልማት አጋር፣ እንዲሁም የልማት ምንጭ ናት። ዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ ስምንት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የልማትና የሰብዕዊ ዕርዳታ ድጋፍ ለአፍሪካ እንደምትሰጥ ይገመታል። ከዚህም ሰፊ ተጠቃሚዎች አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ይነገራል፡፡

በንግድ ግንኙነት ግን ዩናይትድ ስቴትስና አፍሪካ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው፤ አዲስ የተሾሙት አምባሣደሮች ሥራ በስፋት የሚያተኩረውም፤ የንግድ ግንኙነትን በማጠናከር፣ አቅም በመገንባትና የግል ዘርፉን ተሣታፊነት በማጠናከር ላይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

አስተያየቶችን ይዩ (1)

XS
SM
MD
LG