በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"በአማራ ክልል የቀጠለው ውጥረት ዩናይትድ ስቴትስን አሳስቧታል" የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን


ፎቶ ፋይል፦ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
ፎቶ ፋይል፦ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ዓመጽ እየተካሄደበት ባለው በኢትዮጵያ የአማራ ክልልየቀጠለው ውጥረት፣ ዩናይትድ ስቴትስን እንዳሳሰባት ከፍተኛው የሀገሪቱ ዲፕሎማት ትላንት ሰኞ ገለጹ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልል እየጨመረ የሄደው ግጭት እንደሚያሳስባቸው አመልክተው በሀገሪቱ ላሉት ሌሎች ግጭቶችም በፖለቲካዊ ውይይት መፍትሄ መፈለግ እንዳለበት ያሰመሩበት መሆኑን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማት ሚለር ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ባደረጉት ውይይት በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሰፊ የጸጥታ ችግሮችንም መዳሰሱንም የቃል አቀባዩ መግለጫ አመልክቷል፣ ብሊንከን “በኢትዮጵያ መረጋጋትን ለመፍጠር የፖለቲካ ውይይት አስፈላጊነትን አስምረውበታል” ሲሉ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ታጣቂ ቡድን ካለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ ከፌደራል መንግሥቱ ጋራ ግጭት ውስጥ መግባቱ ይታወቃል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ በተጨማሪ በትግራይ ክልል የተጀመረውንና በኋላም ወደሌሎች የሰሜን አኢትዮጵያ አካባቢዎች ተስፋፍቶ ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም የተደረገውን ተኩስ የማቆም የሰላም ስምምነት ሁለተኛ ዓመት በተመለከተ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋራ ውይይት አካሂደዋል።

ብሊንከን ኢትዮጵያ “ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ዩናይትድ ስቴትስ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል” ሲሉም ቃል አቀባዩ ማት ሚለር አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ካለፈው ዓመት ነሀሴ ጀምሮ በአማራ ክልል ያወጀው አስቸኳይ ጊዜ ባለፈው ሰኔ ወር ቢያበቃም ግጭቱ እንደቀጠለ ሲሆን ፌዴራሉ መንግሥት ባለፈው መስከረም ብዛት ያለው ሠራዊት በክልሉ አዝምቷል፡፡

የመብት ቡድኖች እና ዓለም አቀፍ አጋሮቹ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ እያሰሙ ቢሆንም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ባለፈው ወር በፋኖ ታጣቂዎች ላይ ከፍተኛ የጥቃት ዘመቻ ማካሄዱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG