የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ በዐማራ እና በኦሮሚያ ክልል ያለው ኹኔታ አሳስቦኛል፤ ሲሉ እንደተናገሩ፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ቃል አቀባይ ማት ሚለር አስታውቀዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ ትላንት በስልክ የተነጋገሩት ብሊንከን፣ በክልሎቹ ያሉትን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ የፖለቲካ ውይይትንና የሰብአዊ መብቶች መከበር አስፈላጊነትን አጽንዖት እንደሰጡበት ታውቋል። ዓለም አቀፍ ለጋሾች ያቆሙት የምግብ ርዳታም ይቀጥል ዘንድ፣ የሰብአዊ ኹኔታ ቁጥጥር ተሻሽሎ ስለሚቀጥልበትም አሠራር ተወያይተዋል።
እውነተኛ፣ ታማኝ እና ሁሉን አካታች የሽግግር ፍትሕ ሒደትን ለመፍጠር እየተከናወነ ያለውን ሥራ፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመልካም እንደተቀበሉት ተጠቁሟል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በአፍሪካ ቀንድ ስለሚታየው የጸጥታ ተግዳሮት፣ እንዲሁም አንዲት፣ ሰላማዊት እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት ያላቸውን የጋራ ግብ አስመልክቶም እንደተወያዩ ታውቋል።
መድረክ / ፎረም