ዋሺንግተን ዲሲ —
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬዥ ትላንት በኒው ዮርክ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን የደርጅቱ ቃል አቀባይ አስታወቁ።
ዋና ጸሐፊ ጉተሬዥ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ በዚሁ በውይይታቸው በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ እየተካሄዱ ስላሉ አዎንታዊ ለውጦችና በአካባቢው የቀሩትን ፈታኝ ችግሮች ማስወገድ በሚቻሉባቸው መንገዶች ላይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል። በቅርቡ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሰላም ሥምምነት መፈረሙን በደስታ እንደተቀበሉት ገልፀው ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ የዓለሙ ድርጅት ለእነዚህ በጎ ጥረቶችና ኢትዮጵያ በጂቡቲና ኤርትራ መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር በማመቻቸቷ ሙሉ ድጋፍ እንደሚስጥ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ