ቱርክ ውስጥ ደብዛው የጠፋው ሳዑዲ አረቢያዊ ጋዜጠኛ ዣማል ኻሾግዢ ኢስታንቡል በሚገኘው ቆንስላዋ ውስጥ “እዚያ ካገኛቸው ሰዎች ጋር በተፈጠረ ድብድብ ወቅት መሞቱን የምርመራው ቅድሚያ ውጤቶች ያሳያሉ” ስትል ሳዑዲ አረቢያ አስታወቀች።
የሳዑዲ የመንግሥት ቴሌቪዥን የአቃቤ ሕጉን መግለጫ ጠቅሶ ማምሻውን ባወጣው ዘገባ ከኻሾግዢ ሞት ጋር ተያይዞ 18 የሃገሪቱ ዜጎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና የዙፋን ችሎቱ አማካሪ ሳዑድ አል-ቃህታኒ እና የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ኃላፊ አሕመድ አሲሪ ከኃላፊነቶቻቸው መባረራቸውን አመልክቷል።
በኻሾግዢ ሞት ላይ የሚካሄደው ምርመራ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን የአቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
በተጨማሪም የሃገሪቱን የስለላና የመረጃ አገልግሎቶች እንደገና ለማዋቀር በአልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን የሚመራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ እንዲቋቋም ንጉሥ ሳልማን ማዘዛቸውን የመንግሥቱ የዜና አውታር ዘግቧል።
ሪያድ ላይ ቅዳሜ ማለዳ የወጣው ይህ መግለጫ ኻሾግዢ ስለመሞቱ በሳዑዲ አረቢያ የተሰጠ የመጀመሪያ የእምነት ቃል ነው።
ጋዜጠኛው የተገደለው /በኢት.የዘ.አ./ ባለፈው መስከረም 22 ሚስት ለማግባት የሚያስችለውን የጋብቻ ሠነድ ለማውጣት ወደ ኢስታንቡሉ ቆንስላ ቢሮ ከገባ በኋላ መሆኑን የቱርክ ባለሥልጣናት ቀደም ሲል የተናገሩ ቢሆንም ሳዑዲ አረቢያ ግን ኻሾግዢ ከሕንፃው ወዲያውኑ ወጥቷል ስትል ከሦቹን ስታስተባብል ቆይታለች።
ዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት የሳዑዲ አረቢያን የእምነት ቃል ተከትሎ ባወጣው መግለጫ “በኻሾግዢ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚካሄደው ምርመራ ወደፊት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና እስከአሁን በታወቁ ተጠርጣሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም በአድናቆት እንደሚያየው” አስታውቋል።
መግለጫው አክሎም ዩናይትድ ስቴትስ “በዚህ አሳዛኝ አጋጣሚ ላይ እየተካሄዱ ያሉትን ዓለምአቀፍ ምርመራዎች በቅርበት እንደምትከታተልና ወቅቱን ጠብቆ፣ በግልፅና አግባብነት ባለው መንገድ ፍትሕ እንዲሰጥ ትጎተጉታለች” ብሏል።
የሳዑዲ አረቢያ የዛሬው መግለጫ ከመውጣቱ በፊት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በሰጡት ቃል በኻሾግዢ ደብዛ መጥፋት ምክንያት በሳዑዲ አረቢያ ላይ ማዕቀብ ሊጥሉ እንደሚችሉ ተናግረው ነበር። ፕሬዚዳንቱ ዛሬ አሪዞና ውስጥ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ሊከተሉ ስለሚችሉ መዘዞች ለመናገር ጊዜው ገና መሆኑን አመልክተው በመጭዎቹ ቀናት ውስጥ ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።
በኻሾግዢ መጥፋት ምክንያት የሳዑዲ ቆንስላ ሠራተኞችን ዛሬ መመርመሩን የጠቆመው የቱርክ ፖሊስ የቆንሲል ዠነራሉን ሾፌር፣ ቴክኒሻኖችን፣ የሂሣብ ባለሙያዎችንና የስልክ ኦፐሬተሮችን ጨምሮ ከአሥር በላይ ሠራተኞችን ማነጋገሩን የቱርክ መንግሥታዊ የዜና አገልግሎት አናዶሉ ዘግቧል።
ከአሜሪካ ድምጿ ግሬታ ቫን ሰስተርን ጋር ዛሬ፤ ዓርብ ለቃለ-ምልልስ የተቀመጡት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮም በኻሾግዢ ደብዛ መጥፋት ጉዳይ ላይ ተናግረው ነበር።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ቀደም ሲል ሰጥተውት በነበረ መግለጫ የሳዑዲ አረቢያ እጆች በጋዜጠኛው መጥፋት ውስጥ ካሉ “መዘዙ እጅግ የበረታ ይሆናል” ቢሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፖምፔዮ ግን “እነዚያ ምላሾች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ወደዚያ ውስጥ መግባት አልፈልግም። በርግጥ ሊወሰዱ ስለሚችሉ መጠነ-ሰፊ ስለሆኑ ምላሾች ልናስብ እንችላን፤ መደረግ ያለበት ዋናው ጉዳይ ግን የጭብጦቹ መውጣት ነው” ብለዋል።
ከንጉሥ ሳልማንና ከአልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ለመነጋገር በዚህ ሣምንት መጀመሪያ ላይ ወደ ሪያድ ሄደው የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፔዮ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል “ዩናይትድ ስቴትስ ይህንን ጉዳይ የምትይዘው እጅግ በብርቱ መሆኑን በግልፅ ነግሬአቸዋለሁ። ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎችን እንደማንደግፍ፤ እንደዚያ ዓይነት አድራጎቶችን እንደማንቀበል፤ እንዲህ ዓይነት ነገር ከአሜሪካ እሴቶች ጋር እንደማይጣጣሙ፣ እናም አጋጣሚው የተፈጠረው በእነርሱ ቆንስላ ውስጥ በመሆኑ ኃላፊነቱ የእነርሱ መሆኑን ነግሬአቸዋለሁ” ብለዋል።
“ይህንን ጉዳይ ጭብጦቹን በግልፅ በትክክል፣ በተሟላ ሁኔታ፣ በግልፅ፣ ድፍን ዓለም ሊያየው በሚችል መንገድ እስከ ሥረ-መሠረቱ መሄድ የእነርሱ ኃላፊነት ነው። ጭብጦቹን ለይተን ካወቅን በኋላ በሃገሪቱ ውስጥ በማንኛውም ጥፋት ውስጥ የገቡ ሰዎችን በኃላፊነት የመያዝ ኃላፊነትና ቀዳሚ እጅ አላቸው” ሲሉ አክለዋል ፖምፔዮ።
በሌላ በኩል ደግሞ ኻሾግዢ እንዴት እንደተገደለ የሚጠቁም የተቀረፀ ድምፅ ለአሜሪካ ባለሥልጣናት አስደምጠዋል የተባለውን መረጃ የቱርክ ባለሥልጣናት አስተባብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ሰሞኑን ቱርክን የጎበኙ ጊዜ ያንን የተቀረፀ ድምፅ አዳምጠዋል ሲሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።
ፖምፔዮ ወደ ደቡብ አሜሪካ ከመጓዛቸው በፊት በሰጡት ቃል ያዩት ምሥልም ይሁን ፅሁፍ ወይም የሰሙት የተቀረፀ ድምፅ አለመኖሩን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚያገኙትን ማንኛውንም የምርመራም ሆነ የፍለጋ ውጤት ለዓለም እንደሚያሳውቁ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ቻቩሾህሉ ለአናዶሉ የዜና አገልግሎት ዛሬ ገልፀዋል።
በኻሾግዢ ዕጣ ላይ የሳዑዲ አረቢያን መግለጫ አስመልክቶ ዛሬ፤ ዓርብ ማምሻውን አስተያየቶቻቸውን ከሰጡ የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ እንደራሴዎች መካከል የትረምፕ ወዳጅ ናቸው የሚባሉት ሪፐብሊካኑ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሊንድዜይ ግራሃም “አዲሱ የሳዑዲ አባባል አጠራጥሮኛል፤ ስለሚስተር ኻሾግዢ የተባለው ነገር የሆነውን የሚመጥን አይደለም” ብለዋል።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ አመራር አባል የሆኑት ዴሞክራቱ ሴናተር ባብ ሜኔንዴዝ ደግሞ በጋዜጠኛው ሞት ውስጥ እጆቻቸው ባሉ የሳዑዳ ዜጎች ላይ በሰርጌይ ማግኒትስኪ ሕግ መሠረት ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይገባል” ሲሉ በትዊተር ባወጡት መልዕክት አሳስበዋል።
[እአአ በ2012 ዓ.ም.በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የተፈረመው የማግኒትስኪ ሕግ የወጣው ሞስኮ በሚገኝ እሥር ቤት እንዳለ መሞቱ በተገለፀው ሩስያዊ የግብር ሂሣብ ባለሙያ ሰርጌይ ማግኒትስኪ ጉዳይ ሞስኮን ለመቅጣት ታስቦ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ያው ሕግ በመላው ዓለም ሰብዓዊ መብቶችን በሚረግጡ አጥፊዎች ላይ ሁሉ እንዲሠራ ተደረገና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ማዕቀቦችን መጣል፣ ንብረትና ጥቅሞቻቸውን ማገድና ወደ አሜሪካም እንዳይገቡ መከልከል እንዲችል ሥልጣን ሰጠው።]
“ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ “ለአደጋ አጋጠሚዎች” የሚባል የተለየ ሁኔታን አላስቀመጠም። ኻሾግዢ የሞተው በእንካሰላንትያ ግጭት መካከል ቢሆን እንኳ ለመገደሉ ሰበብ ሊሆን አይችልም። ይህ ጉዳይ ከፍፃሜው ገና እጅግ እሩቅ በመሆኑ ዓለምአቀፉ ጫና መቀጠል አለበት” ብለዋል ሜኔንዴዝ በዚሁ የትዊተር መልዕክታቸው።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ