በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሣሙዔል ፈረንጅ አረፈ


ሣሙዔል ፈረንጅ
ሣሙዔል ፈረንጅ

ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ፀሐፌ-ተውኔት፣ ገጣሚ፣ ድምፃዊ፣ ተዋናይ፣ ዲያቆንና የሌሎችም በርካታ ክህሎቶች፣ አስተዋፅዖ፣ ክብርና ሽልማቶች ባለቤቱ ሣሙዔል ፈረንጅ አረፈ።

ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ፀሐፌ-ተውኔት፣ ገጣሚ፣ ድምፃዊ፣ ተዋናይ፣ ዲያቆንና የሌሎችም በርካታ ክህሎቶች፣ አስተዋፅዖ፣ ክብርና ሽልማቶች ባለቤቱ ሣሙዔል ፈረንጅ አረፈ።

ሣሙዔል ፈረንጅ በ81 ዓመት ዕድሜው ለረዥም ዓመታት በኖረባት ቶሮንቶ ካናዳ ከትናንት በስተያ ኅዳር 20/2010 ዓ.ም. ያረፈው ላለፉት 15 ዓመታት በሕክምና ሲረዳ ከቆየ በኋላ ነው።

ነገ፣ ቅዳሜ ኅዳር 23/2010 ዓ.ም. ለአቶ ሣሙዔል ፈረንጅ በቶሮንቶ ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን የፀሎት ሥነ-ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ አስከሬኑ በዲችዉድ መካነ-መቃብር እንደሚያርፍ ቤተሰቦቹ ለቪኦኤ ገልፀዋል።

ከቀኝአዝማች ፈረንጅ ቦቶ እና ከወይዘሮ አበበች ገመዳ በመጋቢት 1929 ዓ.ም. ወለጋ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የተወለደው አቶ ሣሙዔል ቀደም ሲልም በአማርኛና በእንግሊዝኛ ዜና አንባቢነትና በጋዜጠኝነት ሲሠራበት የነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋና ዳይሬክተር ሆኖ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከተሾመበት ጊዜ አንስቶ በማስታወቂያ ሚኒስቴር እና በሌሎችም የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በባለሙያነትና በኃላፊነት አገልግሏል።

ሣሙዔል ለአጭር ጊዜም የቪኦኤ አማርኛ አገልግሎት ባልደረባም ሆኖ ሠርቷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በ1966 ዓ.ም. ተከስቶ ለነበረው ድርቅና ረሃብ ተጎጂዎች ድጋፍ በማሰባሰብ፣ የአክሱም ሃውልት እንዲመለስ በተደረገው ጥረት ውስጥ በመሣተፍና በሌሎችም ጉልህ መድረኮች ውስጥ ተሣትፏል አቶ ሣሙዔል።

ሣሙዔል ፈረንጅ ሁለት መፅሐፎችን የደረሰና ተውኔቶችንም የፃፈ ከመሆኑም በተጨማሪ ስለ ልዕልት ዳያና ሕልፈት በእንግሊዝኛ የፃፈው ግጥም የተለያዩ ዓለምአቀፍ ሽልማቶችን አስገኝቶለታል።

እአአ በጥር 1994 ዓ.ም. ታትሞ የወጣው ታይም መፅሔት የሣሙዔልን መጣጥፎች “የምርጦች ምርጥ” በሚል አምዱ ሥር አስፍሯል።

ሣሙዔል ከኦክላሆማ ገዥ የኦክላሆማ ግዛት፣ እንዲሁም ከጣልያን ፕሬዚዳንት ጁዜፔ ሣራጋት የኢጣልያ የክብር ዜግነት ተሰጥቶታል።

ሣሙዔል ፈረንጅ የስምንት ልጆች አባት፣ የሰባት ልጆች አያት፣ የአንድ ልጅ ቅድም አያት ለመሆን ታድሏል።

ስለ ሣሙዔል ፈረንጅ ወደፊት ዘርዘር ያለ ዝግጅት ይዘን እንመለሣለን።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG