ቅዳሜ ማምሻውን ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የቀድሞ የናሚቢያ የነጻነት ታጋይና መሪ ሳም ኒዮማ የሐዘንና የክብር መግለጫዎች ቀጥለዋል።
የአፍሪካ መሪዎችና የሌሎችም ሀገራት መሪዎች ሐዘናቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
የናሚቢያን የ30 ዓመታት የነጻነት ትግል የመሩት ሳም ኒዮማ፣ ሀገሪቱ በእ.አ.አ 1990 ነጻ መውጣቷን ተከትሎ በተካሄደው ምርጫም የመጀመሪያው መሪ ሆነው ተመርጠዋል። ናሚቢያ በስተመጨረሻ ነጻ ከወጡት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ነች፡፡
ሳም ኒዮማ ‘የደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ሕዝቦች ድርጅት’ ወይም ‘ስዋፖ’ በሚል ምጻር የሚታወቀውን የነጻነት ተጋድሎ ድርጅት ለ47 ዓመታት፣ እንዲሁም ሃገሪቱን ለ15 ዓመታት በፕሬዝደንትነት መርተዋል።
በሶስት የሥልጣን ዘመናቸው የኢኮኖሚ ብልጽግና እና የፖለቲካ መረጋጋት እንዳመጡ ይነገርላቸዋል። በኤድስ ላይ በተከተሉት ፖሊሲም ዓለም አቀፍ አድናቆትን አግኝተዋል።
ለደቡብ አፍሪካ የዘር መድልኦ ሥርዓት (አፓርታይድ) ይሰልሉ ነበር በሚል በአንጎላ የታሰሩ የቀድሞ የስዋፖ አባላት ተሃድሶ እንዲሰጣቸው ባለመፍቀዳቸው ግን ነቀፌታ ቀርቦባቸዋል።
የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በመቃወም፣ ጉዳዩንም “እብደት” ሲሉ በመግለጽ፣ ድርጊቱን የሚፈጽሙትም ተይዘው ከሃገር እንደሚባረሩ በእ.አ.አ 2001 ማስጠንቀቃቸውም የሚታወስላቸው አቋም ነው።
መድረክ / ፎረም