በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በ90 አስገድዶ መድፈሮች ጥፋተኛ የተባለው ግለሰብ በ42 የዕድሜ ልክ እስራቶች ተቀጣ


በደቡብ አፍሪካ በ90 አስገድዶ መድፈሮች ጥፋተኛ የተባለ ግለሰብ በ42 የዕድሜ ልክ እሥራቶች ተቀጥቷል።

የ40 ዓመት ዕድሜ ያለው ንኮሲናቲ ፋካቲ የዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ላይ ጭምር በፈፀመው አስገድዶ መድፈር፣ ሌሎች ልጆች ድርጊቱን እንዲመለከቱ ያስገድድ ነበር ተብሏል። ግለሰቡ ድርጊቱን የፈፀመው ከእ.አ.አ 2012 እስከ 2021 ባለ ጊዜ ውስጥ ከጆሃንስበርግ በስተ ምሥራቅ በምትገኝ መንደር ወዳለ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆችን ዒላማ በማድረግ ነበር።

ሃገሪቱና የተቀረውንም ዓለም ላስደነገጠው ድርጊት የጆሃንስበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግለሰቡን በአስገድዶ መድፈር፣ በጠለፋ ዝርፊያና ጥቃት በመፈጸም ጥፋተኛ በማለት 42 የዕድሜ ልክ እስራቶች ፈርዶበታል።

“ፍርድ ቤቱ፣ በተለይም እንዲህ ዓይነት ወንጀል በወጣቶች እና ራሳቸውን መከላልከል በማይችሉ ልጆች ላይ ሲፈጸም ቅጣት የመስጠት ግዴታ አለበት” ሲሉ ዳኛው ተናግረዋል።

አንዳንዶቹ ሰለባዎቹ ዩኒፎርም እንደለበሱ ወደ ትምህርት ቤት ሲጓዙ ጥቃቱ እንደደረሰባቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ በመኖሪያ ቤታቸው የቤተሰብ ዓባላት እየተመለከቱ ድርጊቱ እንደተፈፀማቸው ዳኛው አስታውቀዋል።

በቁጥጥር ሥር በሚውልበት ጊዜ ለማምለጥ ሲሞክር በፖሊስ እግሩ ላይ በጥይት የተመታው ተከሳሽ፣ በፍርድ አሰጣጡ ወቅት አንገቱን አቀርቅሮ ተስተውሏል።

በደቡብ አፍሪካ ካለፈው ሚያዚያ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ 9ሺሕ 309 አስገድዶ መደፈሮች እንደተፈፀሙ የፖሊስ መረጃ ያሳያል።

መንግስት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቆም በቂ ጥረት አላደረገም ሲሉ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG