ለአያሌ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኝነት ያገለገሉት፣ ሩት ባደር ጊንስበርግ፣ በተወለዱ በሰማኒያ ሰባት ዓመታቸው፣ በካንሰር ህመም ምክንያት፣ ትናንት ዓርብ አርፈዋል፡፡
ከሳቸው በፊት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ለማገልገል የበቁ አንዲት ሴት ብቻ ነበሩ፡፡
ብርቱ የተራማጅ (ሊበራል) አስተሳሰብ አራማጅ እና ለሴቶች መብት ተሙዋጋች፣ የነበሩት የነበሩት ዳኛ ጊንስበርግ ዋሽንግተን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ማረፋቸውን ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በመግለጫው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዋናው ዳኛ ጆን ሮበርትስ ዳኛ ሩት ጊንስበርግን " ሃገራችን ታሪካዊ ሰብዕና ያላቸው ዳኛ አጥታለች" ሲሉ ተናግረውላቸዋል፡፡
ሩት ባደር ጊንስበር በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኝነት እ አ አ ከ 1993 ዓመተ ምህረት አንስተው ለሃያ ሰባት ዓመታት አገልግለዋል፡፡
የህልፈታቸም ምክንያት፣ የሆነው በሰውነታቸው እየተሰራጨ የሄደው የጣፊያ ካንሰር መሆኑን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መግለጫ አመልክቷል፡፡
በተደጋጋሚ በካንሰር ምክንያት ይታመሙ የነበሩት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛይቱ ጊንስበርግ፣ ባለፈ ሃምሌ ደግሞ ጉበታቸውን ታመው የኬሞቴራፒ ህክምና ላይ እንድነበሩ አስታውቀው ነበር፡፡
ካሁን ቀደም ሁለት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን ለሾሙት ለፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ፕሬዚደንታዊ ምርጫው ሊካሄድ ከሰባት ሳምንት ያነሰ ጊዜ በቀረበት ባሁኑ ወቅት፣ የዳኛ ጊንስበርግ ህልፈት ሶስተኛውን በመሾም በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የወግ አጥባቂ ዳኞችን አብላጫነት ለማስፋት ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
የዳኛ ሩት ባደር ጊንስበርግ ህልፈት ፕሬዚደንቱ እሳቸውን የሚተካ ተሹሚያቸውን አጭተው በሪፐብሊካኖች በሚመራው የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የሹመት ማስጸደቂያ ችሎት ማቅረብ ይገባቸዋል፣ ወይስ የጊንስበርግ ወንበር ፕሬዚደንታዊ ምርጫው ተካሂዶ ውጤቱ እስከሚታወቅ ክፍት ሆኖ መቆየት አለበት፣ በሚለው ዙሪያ የፖለቲካ እሰጥ አገባ መቀስቀሱ አይቀርም፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የጊዜ ገደብ የሌለው የዕድሜ ልክ ሹመት ሲሆን ባሁኑ ጊዜ አምስቱን አብላጫ ወንበር የያዙት ወግ አጥባቂ ዳኞች ናቸው፡፡
ናሽናል ፐብሊክ ሬዲዮ ኤን ፒ አር እንደዘገበው ሩት ባደር ጊንስበርግ ከማረፋቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብለው፣ የልጅ ልጃቸው ክላራ ስፔራን ባጻፉዋቸው መግለጫ ላይ " ከሁሉም ትልቁ ምኞቴ አዲስ ፕሬዚደንት እስከሚመረጥ የኔ ተተኪ እንዳይሾም ነው"ብለው ነበር፡፡