በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ ዩክሬን ልቪቭ ከተማ ላይ ብዛት ያለው ሚሳይል ተኩሳለች


በምዕራብ ዩክሬን በልቪቭ በአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ የደረሰው ፍንዳታ እአአ መጋቢት 18/2022
በምዕራብ ዩክሬን በልቪቭ በአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ የደረሰው ፍንዳታ እአአ መጋቢት 18/2022

ዛሬ ሩሲያ ምዕራብ ዩክሬን ልቪቭ ከተማ የአውሮፕላን ጣቢያ አቅራቢያን ዒላማ ያደረጉ በርካታ ሚሳይሎች ተኩሳለች።

በአውሮፕላን ጣቢያው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የከተማዋ ከንቲባ ገልጸው የአውሮፕላን ጥገና ክፍል ግን ተጎድቷል ብለዋል። ዩክሬንን ከፖላንድ ጋር ከሚያዋስነው ድንበር ሰማኒያ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አካባቢ ላይ በደረሰው ጥቃት በሰው ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ለጊዜው የተገኘ መረጃ የለም።

በትናንትናው ዕለት በሩስያ ጥቃት በተመታው የማሪዮፖሉ ህፃናትን ጨመሮ ብዙ መቶ ሰላማዊ ሰዎች የተጠለሉበት የትያትር ቤት ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች እየወጡ ናቸው። ምን ያህሉ በህይወት እንደተረፉ አልታወቀም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዛሬ አርብ ከቻይና ፕሬዚደንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በስልክ እንደሚነጋገሩት ተገልጿል። ባይደን ከቻይናው አቻቸው ጋር የሚነጋገሩት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ዓለም የሩስያን ወረራ ለመመከት ሀገራቸውን እንዲረዳ እየተማጸኑ ባሉበት ባሁኑ ውቅት ሲሆን የሁለቱ መሪዎች ውይይት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ወታደራዊ እርዳታ እንድታደርግ በሩሲያ የተጠየቀችው ቻይና በውጊያው ትልቅ ቦታ እየያዘች መሆኗ ተገልጿል። ለዩክሬን ግዙፉን ወታደራዊ እርዳታ የለገሰች ዩናይትድ ስቴትስ ስትሆን ተጨማሪ ስምንት መቶ ሚሊዮን ዶላር እንደምትሰጥ በዚህ ሳምንት ፕሬዚዳንት ባይደን ይፋ አድርገዋል።

የዋይት ኃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ለጋዜጠኞ በሰጡት ቃል

"ቻይና ከሩሲያ ጎን መሰለፉዋ ያሳደረብንን ጥልቅ ሥጋት በግልጽ አሳውቀናል። ሊያስከትል የሚችለውን ምላሽም ተናግረናል ብለው የዛሬው የስልክ ውይይት ለፕሬዚዳንት ባይደን የፕሬዚዳንት ሺን አቋም ለመገምገም ዕድል ይሰጣቸዋል" ብለዋል። ቻይና የሩስያን አድራጎት አለማውገዟ በራሱ ብዙ ይናገራል ሲሉም ቃል አቀባይዋ አክለዋል።

ውጊያውን በተመለከተ የሩሲያ ኃይሎች ከዩክሬን ኃይሎች በኩል ከከባድ መከታ እየገጠማቸው በመሆኑ በውጊያው ብዙም ሊገፉ የቻሉ አይመስልም ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ባለሥልጣን በሰጡት ቃል ዩክሬንን የከበቡት የሩሲያ ኃይሎች ከሦስት ሳምንትም በኋላ ካሉበት አልገፉም፤ በተለይም ዋና ከተማዋ ኪቭን መጠጋት አልቻሉም ብለዋል። ወታደሮቻቸውን ምግብ እና ትጥቅ ማቅረብ ላይ ተቸግረዋል ነው ያሉት።

የዩናይትድ ስቴትስ እና የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ የዩክሬንን የመከላከያ አቅም የበለጠ ለማጠናከር ስለሚቻልበት መንገድ እየተነጋገሩ መሆናቸው ተመልክቷል። የዋሽንግተን ባለሥልጣናት የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ላይ ውግዘቱን እያፋፋሙት ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን ፕሬዚዳንት ባይደን ፑቲንን የጦር ወንጀለኛ ማለታቸውን እስማማበታለሁ፣ ሲቪሎችን የጥቃት ዒላማ ማድረግ የጦር ወንጀል ነው" ብለዋል።

ለዩክሬን ህዝብ የሜያስፈልገው ህይወት አድን መድሃኒት፣ ሰላም ነው ያሉት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል። ዶ/ር ቴድሮስ የዩክሬን ሰብዓዊ ሁኔታን አስመልክቶ ለተነጋገረው የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ባደረጉት ንግግር

“የውጊያው መራዘም፣ እጅግ ተጋላጩን ህዝብ ስቃይ ከማራዘም በስተቀር ማንንም አይጠቅምም " ብለዋል። በጦርነቱ አርባ ሦስት የጤና ተቁዋማት ላይ ጥቃት መድረሱን ድርጅታቸው እንዳረጋገጠም ገልጸዋል።

በሌላ ዜና የሩሲያ ባለሥልጣናት እና የዜና ማሰራጫዎች ጦርነቱን አስመልክቶ የሚያሰራጩትን የተዛባ መረጃ ቢያጠናክሩም ሰሚ ጆሮ አላገኙም ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG