በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያው ምክር ቤት የኑክሌር ሙከራ እገዳ ስምምነትን የሻረ ሕግ አጸደቀ


የፓርላማ አፈ ጉባኤ ቭያቼስላቭ ቮሎዲን.
የፓርላማ አፈ ጉባኤ ቭያቼስላቭ ቮሎዲን.

የሩሲያ ምክር ቤት፣ አገሪቱ ቀደም ሲል ያጸደቀችውን ዓለም አቀፍ የኑክሌር ሙከራ እገዳ ስምምነት በመሻር፣ ሩሲያ፣ ከምዕራቡ ዓለም ጋራ ውጥረት ውስጥ በገባች ጊዜ፣ የኑክሌር ሙከራ ማድረግ የሚያስችላትን ሕግ በማጽደቅ፣ የፕሬዚዳንት ፑቲንን ፍላጎት እንዳሟላ፣ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

የታችኛው ምክር ቤት ዱማ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሩሲያ ቀደም ሲል ያጸደቀችውን ኹሉን አቀፍ የኑክሌር ሙከራ እገዳ ስምምነት ቀሪ የሚያደርገውን ሁለተኛ እና ሦስተኛ የሕግ አንቀጽ ረቂቅ አጽድቋል።

ሁለቱም አንቀጾች 415 ለዜሮ በኾነ ሙሉ ድምፅ ያለምንም ተቃውሞ እንደጸደቁ ተመልክቷል፡፡

ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ እ.ኤ.አ የ1996 ስምምነትን ብትፈርምም፣ ፈጽሞ ግን ያላጸደቀችውን የዩናይትድ ስቴትስን አቋም “የሚያንጸባርቅ” ሕግ እንዲያጸድቁ እ.ኤ.አ ባለፈው ጥቅምት አምስት ቀን የሩሲያን ምክር ቤት አሳስበው እንደነበር ተገልጿል፡፡

የፓርላማው አፈ ጉባኤ ቭያቼስላቭ ቮሎዲን፣ ሩሲያ ዜጎቿን የመጠበቅ ሓላፊነት እንዳለባት አጽንዖት ሰጥተው፣ እየታየ ለሚገኘው ዓለም አቀፋዊ ውጥረት ዩናይትድ ስቴትስን ተጠያቂ አድርገዋል።

የዱማው ውሳኔ፣ በተለይ ሩሲያ ያላትን የኑክሌር ዐቅም እና የዩክሬንን ወረራ አስመልክቶ ባሉ ዓለም አቀፍ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል፡፡

ሩሲያ፣ የዩክሬኑን ወረራ ባለፈው ዓመት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ፣ ያላትን የኑክሌር ዐቅም፣ ፑቲን ለምዕራቡ ዓለም በተደጋጋሚ ሲያስታውሱ ቆይተዋል፡፡

ፑቲን፣ በዛሬ ረቡዕ የቤጂንግ ጉብኝታቸው፣ የኑክሌር ተኩስ ትዕዛዝ መስጫው ቁልፍ መያዣ ነው፤ የሚባለውን የእጅ ቦርሳ በያዙ የባሕር ኃይል መኰንኖች ታጅበው፣ በመንግሥት ቴሌቪዥን ይታዩ እንደነበር፣ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ዋሽንግተን ካላደረገችው በቀር፣ ሩሲያ የአቶሚክ ሙከራን እንደገና እንደማትጀምር ገልጻለች፡፡

የሩሲያ ምክር ቤት ውሳኔን አስመልክቶ የተናገሩ የኑክሌር መሣሪያዎች ቁጥጥር ባለሞያዎች በአንጻሩ፣ ምዕራባውያን፣ በዩክሬን ጦርነት መካከል ሩሲያ የምታካሒደው የኑክሌር ፍጥጫ አድርገው እንዲያስቡት እየገፋፋች ነው፤ ሲሉ አመልክተዋል፡፡

በሩሲያም ኾነ በዩናይትድ ስቴትስ የሚካሔደው ሙከራ፣ ሌሎቹም ኀይሎች ማለትም ቻይና፣ ሕንድ እና ፓኪስታንም በተመሳሳይ እንዲከተሏቸውና ዐዲስ ዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያዎች እሽቅድድም እንዲሰፍን ያነሣሣል፤ ሲሉ፣ ተንታኞች ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡

በዚኽ ክፍለ ዘመን፣ የኑክሌር ሙከራ የምታደርግ አንዲት ሀገር ብትኖር፣ ሰሜን ኮሪያ ብቻ እንደኾነች ተነግሯል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG