በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የራሽያና አሜሪካ የዲፕሎማሲ ጦርነት ቀጥሏል


በዩናይትድ ስቴትስ የራሽያ አምባሳደር አናቶሊ አናቶኖቭ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በመጭው መስከረም ወር የቪዛ ጊዜያቸው የሚያበቃ 24 የራሽያ ዲፕሎማቶች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መጠየቋን አስታውቀዋል፡፡ውሳኔው የመጣው፣ ሩሲያ በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ የሩሲያ ሠራተኞን፣ ኤምባሲው እንዲያባርር የተገደድበትን ውሳኔ ተከትሎ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ መሆኑም ተነግሯል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባለሥልጣናት 24 የራሽያ ዲፕሎማቶች ከመስከረም 28 በኋላ አሜሪካን ለቀው እንዲወጡ ከመጠየቃቸው በስተጀርባ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ጨዋታ የለም ይላሉ፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሁሉም ነገር ከቪዛ አሰጣጥ እድሳት ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚሰሩ ሁሉም የራሽያ ዲፕሎማቶች በየሶስት ዓመቱ የሚያልፉበት ሂደት መሆኑንም እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡

“ ለራሽያውያኑ በየሶስት ዓመት የሚሰጠው የቪዛ ገደብ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እናንተም እንደምትገምቱት የቪዛው ጊዜያቸው በሚያልቅበት ወቅት እነዚህ ሰዎች ወይም አገሪቱን ለቀው መውጣት ይጠብቅባቸዋል ወይም ለቪዛው እድሳት ማመልከት ይኖርባቸዋል፡፡”ይሁን እንጂ የራሽያ ባለሥልጣናት በአደባባይ ሲናገሩ ዩናይትድ ስቴትስ የቪዛ አሰጣጥ ሂደቱን ጥብቅ በማድረግ ራሽያኑ ከአገር እንዲወጡ እያስገደዱ ነው ብለዋል፡፡


ውሳኔው የመጣው ራሽያ፣ በሞስኮ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሩሲያ ዜጎችንም ሆነ የሌሎች ሶስተኛ ወገን ሠራተኞችን እንዳይቀጥር ገደብ ከጣለች አጭር ጊዜ በኋላ ነው፡፡

በዚያ ውሳኔ መሰረት ዩናትድ ስቴትስ 180 የሚሆኑ የአገር ውስጥ ሠራተኞችን ለማሰናበት ተገዳለች፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት ያ መሆኑን ደግሞ በኤምባሲው ላይ ተጨማሪ ጫናን ፈጥሯል፡፡ ከዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ተቋም ዶናልድ ጀንሰን እንዲህ ያስረዳሉ

“ የቪዛ ጉዳይ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ለራሽያ ተማሪዎች፣ ዩናይትድ ስቴትስን መጎበኝት ለሚፈልጉና ለመሳሰሉት እንደሚደረገው ሁሉ፣ እዚህም ተመሳሳይ ነው፡፡ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመምጣትም ቪዛ ያስፈልጋል፡፡ ለኤምባሲው የሚቀርበው ጥያቄ ብዙ ነው፡፡ በሞስኮ ያለው ትልቅ ኢምባሲ እንኳ ሳይቀር ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልገዋል፡፡ ያ ማለት፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከዚያው ከራሽያ ውስጥ ተገቢውን ማጣራት ካደረገ በኋላ አስፈላጊውን ሥራ የሚሰሩ የራሽያ ዜጎችን ይቀጥራል ማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የቪዛውን ሥራ ያግዛሉ፡፡ በዚያውም ደግሞ በሁለቱ አገሮች መካከል ለሚፈጠር ወዳጅነት እንደ አንድ የማጠናከሪያ መንገድ ሊታይ ይችላል፡፡”

ክሬምሊን ራሽያ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ የሚሰሩ የራሽያ ዜጎችን ፈቃድ እንድምታቆም ያስታወቀችው ባለፈው ሚያዝያ ወር ነበር፡፡

ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስካሁን ደረስ በዋሽንግተን እና ሞስኮ መካከል በአንስተኛ ደረጃ ባሉ ዲፕሎማቶች መካከል ሲደረግ የቆየው ፍልሚያ ከትራምፕ አስተዳደር ጀምሮ የነበረ ነው፡፡

የምልልሱ ፍልሚያ ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው ባለፈው የካቲት መጨረሻ በአሜሪካ የራሽያ አምባሳደር አናቶሊ አናቶኖቭ ወደ ራሽያ ተጠርተው ሄደው ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

ዘግየት ብሎም በራሽያ የአሜሪካ አምባሳደር ጆን ሱልቪያን ተጨማሪ መመሪያ ለመቀበል ወደ ዋሽንግተን እንዲጠሩ ተደርጓል፡፡

ሁለቱም ዲፕሎማቶች ወደ ሥራ ቦታቸው የተመለሱ ፣ እንዲሁም ፕሬዛዳንት ባይደንና ፕሬዚዳንት ፑትን ባለፈው ሰኔ የተገናኘተው የተነጋገሩ ቢሆንም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት አሁንም እንደቀዘቀዘ ነው፡፡

ባለሙያዎች የአሁኑ ሁኔታ በሁለት አገሮች መካከል ያለውን አስቸጋሪ ግ ንኙነት የበለጠ ያባብሰዋል ይላሉ ከአትላንቲክ ካውንስል ጆን ኸርበስት እንዲህ ብለዋል

“የክሬሚልን መንግሥት ፍላጎታችንን የሚቃረን አደገኛ ፖሊስዎችን እያራመደ ነው፡፡ ቀዳሚው እምርጃችን ጠንካራና እነዚህን ፖሊሲዎች በዋናነት ማቆም ይኖርበታል፡፡”

በዲፕሎማሲው መካከል ወዲያና ወዲህ መጓተት ቢኖርም የሞስኮ እና የዋሽንግተን ባለሥልጣናት ግን የሁለቱን አገሮች መካከል ያለውን ስትራቴጂክ ግንኙነት ወደ ላቀና ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ቁርጠኝነቱ ያላቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የቪኦኤ ዘጋቢ ዳሪያ ዴገትስ ከላከችው ዘገባ የተወሰደ፡፡

XS
SM
MD
LG