በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያ ባለስልጣናት በዋግነር ተዋጊዎች ላይ የመሰረቱትን ክስ አነሱ


የሩሲያ የደህንነት አገልግሎት፣ ይቭጌኒ ፕሪጎዣን
የሩሲያ የደህንነት አገልግሎት፣ ይቭጌኒ ፕሪጎዣን

የሩሲያ የደህንነት አገልግሎት፣ ይቭጌኒ ፕሪጎዣን እና እሳቸው የሚመሩት ዋግነር የተሰኘው የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን አባላት በፈፀሙት የትጥቅ አመፅ ዙሪያ የሚያካሂደውን ምርመራ እንደሚዘጋ አስታወቀ። የሩሲያ ዜና ማሰራጫዎች ዛሬ ባስተላለፉት መግለጫ፣ የደህንነት መስሪያቤቱ፣ በአመፁ ላይ የተሳተፉት "ወንጀሉን ለመፈፀም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን አቁመዋል" ብሏል።

ቅዳሜ እለት ታጣቂዎቹን ለፍርድ ላለማቅረብ የተደረሰው ስምምነት የትጥቅ አመፁ እንዲቆም አድርጓል።

ፕሪጎዣን እስካሁን የት እንዳሉ በግልፅ ሳይታወቅ ቢቆይም፣ የበረራ መቆጣጠሪያ ድህረገፆች ከፕሪጎዣን ጋር ግንኙነት ያለው አንድ የጦር አውሮፕላን ማክሰኞ እለት ቤላሩስ ማረፉን አሳይተዋል። በሩሲያ የተካሄደውን አመፅ ለማስቆም በቤላሩስ መሪ አሌክሳንደር ሉኩሼንካ አማካኝነት በተደረገው ድርድር መሰረት የዋግነሩ መሪ ወደ ቤላሩስ ለመሄድ ተስማምተው ነበር።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሰኞ እለት ለሩሲያ ህዝብ ባደረጉት ንግግር የዋግነር አመፅ አስተባባሪዎችን 'ከሀዲዎች' ናቸው ሲሉ ቁጣቸውን ገልፀዋል። የአመፁ አስተባባሪዎች ሞስኮን ለመያዝ ባደረጉት ሙከራ፣ ደቡባዊውን ሮስቶቭ ከተማ ለጥቂት ጊዜ በተቆጣጠሩበት ወቅት፣ የገዛ ወገኖቻቸውን ዋሽተው "ወደ ሞት እና ወደ እሳት እንዲያመሩ፣ የራሳቸው ሰዎች ላይ እንዲተኩሱ" አድርገዋቸዋል በማለት የዋግነር ታዋጊዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

ፑቲን አክለው "አርበኞች" ሲሉ የጠሯቸውን የዋግነር ወታደሮች እና አዛዦቻቸውን ከሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ጋር በመፈራረም ወደ ሩሲያ ጦር ወይም ሌሎች የህግ አስከባሪ ተቋማት ጋር እንዲቀላቀሉ የጋበዟቸው ሲሆን፣ ወደ ቤተሰቦቻቸው እና ወደ ጓደኞቻቸው የመመለስ ወይም ወደ ቤላሩስ መሄድ ከፈለጉም በነፃነት የመሄድ ምርጫ ሰጥተዋቸዋል።

በሩሲያ ወታደራዊ አመራር ላይ ከተካሄደው አጭር አመፅ በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኞ እለት በቴሌግራም የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ የድምፅ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሪጎዣን፣ "ነባሩን ስርዓት እና በህጋዊ መንገድ የተመረጠውን መንግስት የማፍረስ አላማ አልነበረንም" ያሉ ሲሆን ይልቁንም "የፍትህ ጉዞ" ሲሉ የጠሩትን ድርጊት የፈፀሙት የሩሲያ ጦር በግል ጦራቸው ላይ በፈፀመው ጥቃት ነው ብለዋል።

የዋግነሩ መሪ የሩሲያ ጦር የዋግነርን የጦር ካምፕ በሚሳይል እና በሄሊኮፕተር በማጥቃት ወደ 30 የሚጠጉ ተዋጊዎቹን እንደገደለ የሚከሱ ሲሆን፣ ሩሲያ ግን ክሱን አትቀበልም።

XS
SM
MD
LG