በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያ አምባሣደር ገዳይ “አሌፖን አትርሱ …” እያለ ይጮኽ ነበር


በቱርክ የሩሲያ አምባሣደር የነበሩትን አንድሬ ካርሎቭን የገደለው ሲቪል የለበሰና ተረኛ ያልነበረ የፖሊስ አባል “አሌፖን አትርሱ! ሶርያን አትርሱ! የእኛ ሃገሮች ደኅና እስካልሆኑ እናንተም ደኅና አትሆኑም!” እያለ ይጮኽ እንደነበረ እማኞች ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡

የፖሊስ አባሉ ወደ መድረክ ወጥቶ ተኩስ በከፈተባቸው ወቅት አምባሣደሩ በሩስያ ኤምባሲ በተዘጋጀ “ሩሲያ በቱርካዊያን ዐይን” የተባለ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ላይ ንግግር እያደረጉ ነበር፡፡

“ሩሲያ ሶሪያ ውስጥ ገድላቸዋለች” ስላላቸው ንፁሃን ሰዎች እንደሚበቀል ገዳዩ ሲዝት እንደነበርም ታውቋል፡፡

በተተኮሰባቸው ጥይት ክፉኛ የቆሰሉት አምባሣደር ካርሎቭ የመድረኩ ወለል ላይ ወድቀው እያጣጣሩ ሳሉ ተኳሹ የያዘውን ሽጉጥ ወደ ጣሪያና አንድ ጊዜም ወደ ታዳሚው ሰው ሲያዞር ታይቷል፡፡

በሥፍራው የነበሩት ኃይሎች ጥቃት አድራሹን የሃያ ሁለት ዓመት ሰው ማቭሉት ሜርት አልቲንታስን ተኩሰው ከመግደላቸው በፊት ሌሎች ሦስት ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡

አድራጎቱን “የሽብር ጥቃት” ሲሉ ወዲያው ያወገዙት የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ቱርክ ገዳዩን የላኩ ሰዎች ይኖሩ እንደሆነ የቱርክ መንግሥት በአፋጣኝ እንዲያጣራ አሳስበው የአንካራ ባለሥልጣናት በሩሲያ የዲፕሎማሲ ተቋማት ዙሪያ ያለውን የፀጥታ ጥበቃ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በአምባሣደሩ ላይ የተፈፀመውንጥቃት በብርቱ እንደሚያወግዝ የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ እና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ ዛሬ ገልፀዋል፡፡

“ይህ በዲፕሎማቲክ ኮር አባል ላይ የተፈፀመ አረመኔአዊ ጥቃት ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑ ባሻገር በማንኛውም መልክ የሚፈጠር ሽብር ፈጠራን ለመጋፈጥ ባለን ቁርጠኝነት ከሩሲያና ከቱርክ ጋር በኅብረት እንቆማለን” ብለዋል የዋይት ሃውሱ ኔድ ፕራይስ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም የአምባሳደር አንድሬ ካርሎቭን ግድያ “የሠለጠነ ሥርዓትን ሕግጋት ሁሉ የጣሰ አድራጎት” ሲሉ ውግዘታቸውን አሰምተዋል፡፡

አምባሳደሩን የገደለው የፖሊስ አባል “ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንደሚኖሩ የሚነገረውምና ቱርክ ውስጥ ባለፈው ሐምሌ የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት ካውጠነጠኑ ሰዎች አንዱ ናቸው የሚባሉት ሙስሊም የሐይማኖት መሪ ፌቱላህ ጉለን ተከታይ ለመሆኑ ጠንካራ ምልክቶች አሉ” ሲሉ አንድ የቱርክ መንግሥት ባለሥልጣን ተናግረዋል፡፡

የቱርክ የጦር ጄቶች ባለፈው ዓመት የሩሲያን ቦምብ ጣይ ጄት መትተው ከጣሉ ወዲህ ሻክሮ የነበረው የሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት ቀስ በቀስ መሻሻል እያሳየ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡

በከፊል የሩሲያ የጦር ጄቶች በሶሪያ አማፂያን ላይ እያደረሱ ነው በሚባለው ተከታታይ ድብደባ ምክንያት ተባብሷል ለሚባለው የአሌፖ የስደት ቀውስ መፍትኄ ለመሻት ሩሲያና ቱርክ በቅርበት እየሠሩ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡

XS
SM
MD
LG