በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እህል ከዩክሬን እንዲወጣ የሚያደርገው ሥምምነት እንዲታደስ ተመድ ጠየቀ


ፎቶ ፋይል - የጭነት መኪናው እህል ሲያወርድ ዩክሬን 7/9/2022
ፎቶ ፋይል - የጭነት መኪናው እህል ሲያወርድ ዩክሬን 7/9/2022

እህል በጥቁር ባህር ወደቦች በኩል ከዩክሬን እንዲወጣ ያስቻለውና ከሞስኮ ጋር የተደረሰው ሥምምነት የግዜ ገደብ ሊያበቃ በተዳረሰበት ዋዜማ ባለፈው ዓርብ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ሃላፊ ሥምምነቱ እንዲራዘም ጠይቀዋል። የሥምምነቱ መራዘም ዓለም አቀፍ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥና የእህል ዋጋን ለማረጋጋት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩሲያ አምባሳደር በበኩላቸው ሞስኮ ሥምምነቱን ለማደስ ዝግጁ ብትሆንም፣ የምታድሰው ለ60 ቀናት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም መራዘም ከነበረበት 120 ቀናት ግማሹ መሆኑ ነው።

ባለፈው ሐምሌ በቱርክና በተመድ አደራዳሪነት ከሩሲያና ዩክሬን ጋር ለ120 ቀናት የተደረሰው ሥምምነት የዓለም የዳቦ ቅርጫት ከሆነችው ዩክሬን በጥቁር ባህር በኩል እህልና ማዳበሪያ እንዲወጣ አስችሏል። የመጀመሪያው ሥምምነት ባለፈው ህዳር ለ120 ቀናት ታድሶ የነበረ ቢሆንም ባለፈው ቅዳሜ አብቅቷል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩሲያ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዚያ እንዳሉት የሥምምነቱን ውጤታማነት ለመገምገም ክሬምሊን የግዜ ርዝመቱን ማሳጠር እንደምትሻ ተናግረዋል።

የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርቲን ግሪፊት በጸጥታው ም/ቤት ሲናገሩ እንዳሉት ከዮክሬን የወጣው እህል በዓለም የእህል ዋጋ እንዲቀንስ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ካለፈው ነሐሴ ወዲህ 25 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እህል ከዩክሬን መውጣቱን ግሪፊት ጨምረው ገልጸዋል።

ሥምምነቱ ባለፈው ሐምሌ ከተፈረመ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እና ሌሎች በድርቅ ወደተጠቁ አገራት በመቶ ሺህ ቶን የሚቆጠር ስንዴ መላኩ ይታወቃል፡፡

XS
SM
MD
LG