በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩክሬን የጦር ማጓጓዣ አውሮፕላን በመጣል 65 ምርኮኞችን ገድላለች - ሩሲያ


አውሮፕላኑ ቤልጎርድ ግዛት በያብሎኖቮ አቅራቢያ በሚገኝ የመኖሪያ አካባቢ ሲከሰከስ የሚያሳይ ምስል
አውሮፕላኑ ቤልጎርድ ግዛት በያብሎኖቮ አቅራቢያ በሚገኝ የመኖሪያ አካባቢ ሲከሰከስ የሚያሳይ ምስል

የዩክሬን ኃይሎች አንድ ወታደራዊ መጓጓዣ አውሮፕላን መትተው በመጣል በውስጡ የነበሩ 65 ዩክሬናውያን የጦር ምርኮኞችን ጨምሮ 74 ሰዎችን ገድለዋል ሲል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ከሷል፡፡

ዩክሬናውያኑ ምርኮኞች የጦር እስረኞች ልውውጥ አካል በመሆን የሩሲያው ክልል ወደ ሆነው ቤልጎርድ ግዛት በመጓዝ ላይ እንደነበሩ የሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል፡፡

ከ65ቱ የጦር ምርኮኞች በተጨማሪ ኢል-76 የተሰኘው የማጓጓዣ አውሮፕላን፣ ስድስት የአውሮፕላኑን ሠራተኞችና ሌሎች ሦስት መንገደኞችን አሳፍሮ እንደነበርም የመከላከያ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በአውሮፕላኑ ላይ የተሳፈሩት እነማን እንደነበሩ ማረጋገጥ አለመቻሉን የጠቀሰው የአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ፣ የኪየቭ ባለሥልጣናት ያልተረጋገጠ መረጃን ከማጋራት መቆጠብ እንደሚገባ ከማስጠንቀቅ በቀር ስለ አደጋው አስተያየት አለመስጠታቸውን ገልጿል፡፡

የአደጋው መንስኤ ግልፅ ባይሆንም፣ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የወጣው የቪዲዮ ምስል አደጋው በደረሰበት ቦታ የእሳት አደጋ መከሰቱን አሳይቷል።

የዩክሬን ኃይሎች አውሮፕላኑን በሚሳዬል መትተው ጥለዋል ያለቸው ሩሲያ ድርጊቱን “የሽብር ተግባር” ብትለውም ምንም አይነት ማስረጃ አለማቅረቧን ዘገባው አመልክቷል፡፡

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴሩ መግለጫ ከቤልጎሮድ አዋሳኝ ከሆነው የዩክሬን ካርኪቭ ክልል ሁለት የዩክሬን ሚሳኤሎች ሲወነጨፉ የሩሲያ ራዳር መመልከቱን አስታውቋል፡፡

ክስተቱ የተፈጠረው ድንበር ተሻጋሪ ውጥረቶች እና ግጭቶች በቀጠሉበት ወቅት ሲሆን፣ ሩሲያ የጠበቀችውን የአየር የበላይነትን ማግኘት አለመቻሏ ችግር ውስጥ የከተታት መሆኑ በዘገባው ተመልክቷል፡፡ ዩክሬን የሩሲያ አውሮፕላኖችን በማውደም የቅርብ ጊዜ ስኬት አስመዝግባለች፡፡

ሁለቱም ሀገራት የረዥም ርቀት ጥቃቶችን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሩሲያ ከውጭ ተጨማሪ ሚሳኤሎችን ስትሻ፣ ዩክሬን ደግሞ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ርዳታ እያገኘች እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG