በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ አህጉር አቋራጭ ሚሳይል ተኩሳብናለች" - ዩክሬን


የሩሲያ የሚሳኤል ጥቃት ከተፈፀመበት ሥፍራ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ቃጠሎውን እያጠፉ፤ በዲኒፕሮ፣ ዩክሬን እአአ ኅዳር 21/2024
የሩሲያ የሚሳኤል ጥቃት ከተፈፀመበት ሥፍራ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ቃጠሎውን እያጠፉ፤ በዲኒፕሮ፣ ዩክሬን እአአ ኅዳር 21/2024

ሩሲያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2022 ወረራ ከከፈተች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳይል እንደተኮሰችባት ዩክሬን ዛሬ ሐሙስ አስታወቀች፡፡

የዩክሬን የአየር ሃይል ከድምጽ በአምስት እጥፍ ይፈጥናል የተባለውን “ሃይፐርሶኒክ ሚሳይል እና ሰባት ክሩዝ ሚሳይሎችን ያካተተው መጠነ ሰፊ የሚሳይል ጥቃት የተተኮሰው ከሩሲያ አስትራካን ክልል ነው” ብሏል፡፡

ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮኖች) እና መድፎች የካተተው የሚሳይል ጥቃቱ የኢንዱስትሪ ስፍራዎችን ጨምሮ ዩክሬን ያሉ የተለያዩ ይዞታዎች ላይ ያነጣጠረ እንደነበረ ተነግሯል፡፡

የዩክሬን ባለሥልጣናት በሩሲያ የአየር ጥቃት በዲኒፕሮ ፔትሮቭስክ ክልል በሚገኝ የኢንዱስትሪ አካባቢ ከባድ ጉዳት መድረሱን ዛሬ ሐሙስ ተናግረዋል።

ሩሲያ ስለ ዩክሬን መግለጫ ወዲያኑ አስተያየት አልሰጠችም፡፡

ኒውክሊየር ጦር ቦምብ መሸከም የሚችለው የሩሲያ አህጉር አቋራጩ የረዥም ርቀት ሚሳይል (ICBM) የተተኮሰው ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ ዩክሬን ሩሲያ ድንበር ውስጥ ዘልቃ ዒላማዎችን ለማጥቃት የረጅም ርቀት ሚሳይሎቻቸውን እንድትጠቀም ከፈቀዱ ከቀናት በኋላ ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ የዩክሬን ወታደሮች እየገፋ የመጣውን የሩሲያ እግረኛ ሠራዊት መክተው ለመመለስ እንዲችሉ ለመርዳት የሚቀበሩ ፈንጂዎችን ለመላክ ማቀዷን የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን ትላንት ረቡዕ አስታውቀዋል፡፡

ሥልጣናቸው ሊያበቃ የሁለት ወር ጊዜ የቀራቸው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቀደመውን አቋማቸውን ቀይረው ዩክሬን ዋሽንግተን የተሰጠቻትን የረዥም ርቀት ሚሳይሎችን ተጠቅማ ወደሩሲያ ግዛት ዘልቃ እንድታጠቃ የፈቀዱ ሲሆን ይሄኛው ውሳኔ በቅርብ ቀናት ውስጥ ሁለተኛው የአሜሪካ ፖሊሲ ለውጥ መሆኑ ተመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG