የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስትን “የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩሲያ ውስጥ መኖራቸውን የሚያሳይ ማስረጃ አለ” ሲሉ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ትላንት ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል “ቀሪው ነገር” እዚያ ምን እንደሚሠሩ ማየቱ ነው ብለዋል።
ኦስትን ይህን ያሉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ሁለት የሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ክፍሎች ሩሲያ ውስጥ ለዩክሬኑ ጦርነት ሊውል የሚችል ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑን መንግሥታቸው መረጃ እንዳለው ከተናገሩ አንድ ቀን በኋላ ነው፡፡
ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ "የተጠናከረ ግንኙነት" አላቸው ያሉት ኦስትን ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሣሪያ እንደሰጠች ጠቁመዋል፡፡
"ግንባር ከፈጠሩ፣ አላማቸው በዚህ ጦርነት ሩሲያን ወክለው ለመሳተፍ ከሆነ፣ ያ በጣም፣ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፣ በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በህንድ እና ፓሲፊክ ውቅያኖስ አካባቢ (ኢንዶ-ፓሲፊክ) ባሉ ጉዳዮችም ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል" ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኦስትን ሩሲያ እ.ኤ.አ. በ2022 መጀመሪያ ላይ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ በመውረር በከፈተችው ጦርነት ሰለባ ስለሆኑ ሩሲያውያን ገልፀው፣ የሰሜን ኮሪያ እዚህ ውስጥ መጨመር የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ብዙ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ የበለጠ ችግር ውስጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላካች ነው” ብለዋል።
ዜሌነስኪ "ሰሜን ኮሪያ በአውሮፓ ጦርነት ውስጥ ጣልቃ መግባት ከቻለች፣ በዚህ አገዛዝ ላይ የሚደረገው ጫና በእርግጠኝነት በቂ አይደለም ማለት ነው" በማለት ዩክሬን ከዓለም ጠንካራና ተጨባጭ ምላሽ ትጠብቃለች” ብለዋል፡፡
መድረክ / ፎረም