ሞስኮ እንዳስታወቀችው ትልቋ የጦር መርከቧ ትናንት ሃሙስ በእሳት ቃጠሎ ምክንያት ፍንዳታ ከደረሰባት በኋላ ወደወደቡ እየተሳበች ሳለ ሰጥማለች።
የዩክሬን ባለሥልጣናት የሩሲያን ሚሳይል ተሸካሚዋን ሞስክቫን በሚሳይል መትተናታል ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጃን ከርቢ በበኩላቸው የጦር መርከቧ በዩክሬን ሚሳይል መመታቷ አለመረጋገጡን ነው የገለጹት።
ግዙፏ ሞስክቫ አንድ መቶ ሰማኒያ ስድስት ሜትር ርዝማኔ ያላት ሲሆን የሩሲያ የባህር ኃይል ካሉት ሦስት ብቻ መሰል የጦር መርከቦች አንዷ እንደነበረች ጠቅሰው ከአሁኑ ወቅት አኳያ አቅማቸው እንደሚጎዳ የታወቀ ነው። በባህር ኃይላቸው አቅም ላይ ለዘለቄታው ምን ዓይነት ጉዳት ያስከትላል የሚለውን ግን አሁን ለጊዜው ግልጽ አይደለም ብለዋል።
ተንታኞች እንደሚሉት ግን የማያጠራጥረው ከዩክሬን ጋር ጦርነት ላይ ላለችው ለሩሲያ ዝነኛዋን የጦር መርከቧን ማጣት ከባድ የስነ ልቦና ጉዳት መሆኑ ነው። በወታደራዊ ኃይል የምትበልጣትን ጠላቷን ጥቃት በመመከት ለምትዋጋው ለዩክሬን ደግሞ አስደናቂ ክንዋኔ አስመዝግቦላታል።
ሩሲያ መርከቡ ወደወደቡ በመወሰድ ላይ ሳለ ሰጠመ ከማለት በስተቀር በሚሳይል መመታቱን አላረጋገጠችም። ሩሲያ ለበቀል በሚመስል እርምጃ ዛሬ ጠዋት ኪቭ የሚገኝ ፀረ መርከብ ሚሳይል አምራች እና ጥገና ፋብሪካ ላይ የሚሳይል ጥቃት አድርሳለች።
የዩክሪን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘሌንስኪ በሌሊት መግለጫቸው "እናንት የሩሲያንም መርከብ ማስጠም እንደሚቻል ያሳያችሁ ናችሁና አከብራችኋለሁ" ብለዋል።