ዩክሬን የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ተጠቅማ በሞስኮ እና በካሉጋ ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ለማድረስ ሞክራ ነበር ስትል ሩሲያ አስታወቀች፡፡
ባለሥልጣናቱ አክለውም “ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን የአየር መከላከያ ኃይሎቻችን መትተው ጥለዋቸዋል” ብለዋል፡፡ ስለደረሰ ጉዳት ግን የተዘገበ ነገር የለም፡፡
ዩክሬን በተሰነዘረው በዚህ የአየር ጥቃት በበርካታ የሩስያ የአውሮፕላን ጣቢያዎችን የበረራ እንቅስቃሴዎች አስተጓጉሎ እንደነበር ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን መልሶ መቀጠሉ ታውቋል፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን አንዱ በሌላው ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ሲያደርሱ የቆዩ ሲሆን፤ በአብዛኛውም ተመትተው የወደቁ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ስብርባሪ ጉዳት ይደርሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዴንማርክ እና ኔዘርላንድስ “ዩናይትድ ስቴትስ ሰራሽ ኤፍ 16 ተዋጊ ጀቶችን ለዩክሬን ኃይሎች እንሰጣለን” ሲሉ ትናንት አስታውቀዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ዛሬ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ለዴንማርክ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር ምስጋና አቅርበዋል።
የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት ፍሬደሪክሰን ሀገራቸው 19 ኤፍ 16 ጀቶች ለዩክሬን እንደምትሰጥ ገልጸው ስድስቱ በአውሮፓውያኑ 2024ዓም መጀመሪያ ላይ ይደርሳሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡
የኔዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩተ በበኩላቸው ሀገራቸውን ምን ያህል ኤፍ 16 ጀቶች ለዩክሬን እንደምትለግስም ሆነ መቼ እንደሚደርሱ በውል አላስታወቁም፡፡ የሚወስነው የዩክሬን የአየር ኃይል እና የመሰረተ ልማት ዝግጁነት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት አስተያየት የተዋጊ ጀቶቹ መላክ ጦርነቱ ያለበትን ይዞታ በቅርብ ጊዜ የሚለውጥ አይመስልም፡፡
ባለፈው አርብ የዩናይትድ ስቴትሱ ጀነራል ጄምስ ሄከር ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፡ ባሁኑ ጊዜ ሩሲያም ሆነች ዩክሬይን በአየር ውጊያ የበላይነት የሚይዙበት ሁኔታ አይኖርም ብለዋል፡፡ ጀኔራሉ ከአሜሪካ ድምጽ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ከየብስ ወደ አየር ተተኳሽ ሚሳይሎች በብዛት እስካሉ ድረስ በአየር ውጊያ ማንኛውም ወገን የበላይነት ማግኘት የሚችል አይመስለኝም” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
መድረክ / ፎረም