በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

‘ሩሲያ የአውሮፓ ሀገራትን ለማተራመስ የሚረዳ አቅም ግንባታ ይዛለች’ ሲል አዲስ አዲስ ሪፖርት አመለከተ


ፎቶ ፋይል፦ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን
ፎቶ ፋይል፦ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ሩሲያ የአውሮፓ ሀገራትን ማተራመስ የሚያስችላት እና እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ያላትን ተጽዕኖ ለማጠናከር አቅም በመገንባት ላይ ትገኛለች” ሲል አንድ ዋና መቀመጫውን በብሪታንያ ያደረገ የጥናት እና ምርምር ተቋም በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል። ይህም ‘ለሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አገሮች ህብረት - ኔቶ እና ትኩረታቸውን በዩክሬኑ ጦርነት ላይ ላደረጉት አባል ሃገሮቹ ስትራተጂያዊ ስጋት የሚደቅን ድርጊት ነው’ ብሏል።

‘ዘ ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት’ የተባለው የጥናት ተቋም ተመራማሪዎች ባወጡት በዚህ ጥልቅ ግምገማ ያዘለ ሪፖርታቸው፣ ‘አገራቱ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ወረራ በብቃት መመከት ይቻላቸው ዘንድ፡ ሞስኮ እያካሄደች ያለውን መደበኛ ያልሆነ ጦርነትም ለማምከን ብዙ ጥረት ማድረግ አለባቸው’ ሲሉ ሞግተዋል።

“የዩክሬኑ ጦርነት እየገፋ እና እየተወሳሰበ በሄደ ቁጥር ሩስያ ተጨማሪ ቀውሶችን የመፍጠር ፍላጎት አላት” ሲሉም ጃክ ዋትሊንግ፣ ኦሌክሳንደር ቪ. ዳኒሊዩክ እና ኒክ ሬይኖልድስ የተባሉት የጥናት ጽሁፉ አቅራቢዎች ‘ባልካንን ለጥፋት የተመቻቸ ግዛት’ ባሉት ጽሁፋቸው አስረድተዋል። እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1831 የተመሰረተው የጥናት ተቋም ያቀረበው 35 ገጾች ያሉት የጥናት ሪፖርት ይፋ የተደረገው ሩስያ በዩክሬን ላይ ይፋ ወረራ የፈጸመችበት ሁለተኛ ዓመት ሊከበር ጥቂት ቀናት ሲቀሩት መሆኑ ነው።

ሩስያ ካሁን ቀደም እንደ ሞልዶቫ ያሉ ሃገሮችን ለማተራመስ ያደረገቻቸው ጥረቶች በተፈጠሩ አንዳንድ የፀጥታ ክፍተቶች እና የክሬምሊን የደህንነት ሰራተኞች በሙሉ ተጠራርገው በመውጣታቸው ባይሳኩላትም፤ ‘የሩስያ ጦር ሰራዊት በአሁን ወቅት ግን መደበኛ ያልሆኑ ጥቃቶችን መሰንዘር የሚያስችለውን አቅም እያጠናከረ ነው’ ሲል ሪፖርቱ አመልክቷል። "ሩሲያ የዩክሬንን አጋሮች የማናወጥ ፍላጎት አላት” ያለው ሪፖርት አክሎም፤ “በመላው አውሮፓ በሚደረጉት ምርጫዎች ላይ በዜጎች እና በቡድኖች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ለማባባስ እና ሁከቶችን ለመፍጠር የሚያስችሉ በርካታ እድሎች ይኖራሉ" ብሏል።

ሪፖርቱ ከሩስያ የደህንነት መሥሪያ ቤት የተገኙ ሰነዶችን እና እንዲሁም በዩክሬንና በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ከሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር ያካሄዷቸውን ቃለ-ምልልሶች በመንተራስ፡ ‘ሩስያ ከዩክሬኑ ግጭት ባሻገር’ ተጽእኖዋን ለማስፋት የያዘችውን ጥረት የሚዘረዝር መረጃ አቅርቧል። "ከዩክሬን የሚሻገረው የሩስያ ኢላማ፣ አገራቱ ባላቸው ንቁ የትብብር እንቅስቃሴዎች ላይም የተነጣጠረ ነው" ሲል ሁኔታው ደቅኖታል ያለውን ብርቱ ስጋት ለመመከት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ “ያልተቋረጠ የጥንቃቄ ጥረት መደረግ አለበት” ሲል አሳስቧል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG