ሩሲያ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በዩክሬን ባካሄደችው የአየር ድብደባ በዋና ከተማው የሚገኘው የህፃናት ሆስፒታል በሚሳይል መመታቱ ተገለጸ። በአየር ጥቃቱ ቢያንስ 20 ሰዎች ተገድለዋል።
የነፍስ አድን ሠራተኞች ኪቭ የሚገኘውን ኦክማትዲት የህፃናት ሆስፒታል ፍርስራሽ እየቆፈሩ መሆኑን እና የተጎጂዎች ቁጥር እስካሁን እንዳልታወቀ፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ ተናግረዋል።
"ሩሲያ ሚሳይሎቿ የሚያርፉበትን ቦታ እንደማታውቅ ልትሆን አትችልም። ለፈጸመችው ወንጀል ሁሉ ተጠያቂ መሆን አለባት" ሲሉ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው የፃፉት ዘለንስኪ፣ "ዓለም በዚህ ጉዳይ ላይ ዝም ማለት የለበትም፣ ሩሲያ ምን እያደረገች እንደሆነ ማየት አለበት" ብለዋል።
የኪቭ ከተማ ወታደራዊ አስተዳደር በበኩሉ በሩሲያ ጥቃት ቢያንስ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን እና በበርካታ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ህንፃዎች መጎዳታቸውን ተናግረዋል።
የሩሲያ ጥቃት የዘለንስኪ የትውልድ ከተማ በሆነችው ክሪቪ ሪህ ከተማ ውስጥም ቢያንስ አስር ሰዎች መግደሉን እና ሌሎች 31 ሰዎች መቁሰላቸውን፣ የከተማዋ ወታደራዊ አስተዳደር ኃላፊ የሆኑት ኦሌክዛንደር ቪልኩል ተናግረዋል።
በምስራቃዊው የዩክሬን ክልል በምትገኘው ዶኔስክ ክልል የሚገኝ የኢንዱስትሪ ፋብሪካም በሚሳይ መመታቱን እና ቢያንስ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም