የአፍሪካ ሀገሮችን ፕሎማሲያዊ ድጋፍ ለማሰብሰብ ጥረት እያደረገ ያለው የሩሲያ መንግሥት ለማላዊ 20 ሺህ ቶን ማዳበሪያ መለገሷ ተዘገበ።
በማላዊ የሩሲያ አምባሳደር ኒኮላይ ክራስሊንኮቭ ትናንት ሰኞ በመዲናዋ ሊሎንግዌ በተካሄደው የርክክብ ስነ ስርዐት ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው ለአፍሪካ ሀገሮች 260 ሺህ ቶን ማዳበሪያ እንደምትለግስ ገልጸዋል።
የሩስያው አምባሳደር አክለውም በመጪው ሃምሌ ወር ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ላይ በሚከፈተው በሁለተኛው የሩሲያ እና የአፍሪካ ጉባዔ ላይ የሚካፈሉ የአፍሪካ መሪዎች ሩሲያ ላይ የተጣሉት ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች እንዲነሱ ግፊት እንደሚያደርጉ ተስፋ አለኝ ብለዋል።
ለማላዊ የማዳበሪያውን ስጦታ የለገሰው ኡራልቼም ኡካልካይ የተባለው የሩስያ የማዳበሪያ አምራች ድርጅት መሆኑ ተገልጿል።
የማላዊ የግብርና ሚኒስትር ሳም ካዋሌ የማዳበሪያው ዕርዳታ አራት መቶ ሺህ አርሶ አደር አባወራዎች ምርታቸውን እንዲያሳድጉ ለመርዳት እንደሚውል መናገራቸውን የአሶሲየትድ ፕሬስ ዘገባው አመልክቷል።