በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ ሁለተኛ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ አሰረች


ጋዜጠኛ አልሱ ከርማሺቫ
ጋዜጠኛ አልሱ ከርማሺቫ

የዩናይትድ ስቴትስ ህግ አውጪዎች እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ሩሲያ ሁለተኛ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ አስራለች በማለት ወቀሳ አቅርበዋል።

ሩሲያ ለነፃ አውሮፓ ድምፅ እና ነፃነት ራዲዮ የምትሠራውን ጋዜጠኛ ማሰሯን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት አብላጫ መቀመጫ ያለው የዴሞክራት ፓርቲ መሪ ቸክ ሹመር ሐሙስ ዕለት መግለጫ አውጥተዋል።

አልሱ ከርማሺቫ የተባለቸው፣ የአሜሪካ እና ሩሲያ ጥምር ዜግነት ያላት ጋዜጠኛ የተከሰሰችው፣ በውጭ መንግሥት ወኪልነት አልተመዘገበችም በሚል ነው። ጋዜጠኛዋ በቤተሰብ ውስጥ ባጋጠማት አስቸኳይ ችግር ምክንያት ወደ ሩሲያ የተጓዘችው በግንቦት ወር ሲሆን፣ በሰኔ ወር አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ለአጭር ግዜ ተይዛ ፓስፖርቷ ተወስዷል።

ከርማሺቫ ረቡዕ ዕለት የታሰረች ሲሆን ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች እስከ አምስት አመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ይጠብቃታል። ሩሲያ፣ እ.አ.አ በ2020 በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የሚደገፈውን የነፃ አውሮፓ ድምፅ እና ነፃነት ራዲዮ በውጭ መንግስት ወኪልነት ሰይማለች።

በገለልተኝነት የሚንቀሳቀሰው መገናኛ ብዙሃን በበኩሉ፣ በዜና ስርጭት ስራው ላይ ጣልቃ ገብነት እንደሆነ እና የዜና ማሰራጫ ስራውን እንደሚገድብበት በመግለፅ፣ ስያሜውን አልተቀበለውን።

እስሩን ተከትሎ፣ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ እህት ሚዲያ ተቃም የሆነው የነፃ አውሮፓ ድምፅ እና ራዲዮ ሊብረቲ ባወጣው መግለጫ፣ ከርማሺቫ በአስቸኳይ ከእስር እንድትለቀቅ እና ወደ ቤተሰቧ እንድትመለስ ጠይቋል።

ሲፒጄ የአሜሪካ እና ሩሲያ ጥምር ዜግነት ያላት ጋዜጠኛ አልሱ ከርማሺቫ በተሳሳተ የወንጀል ክስ መታሰሯ በእጅጉ አሳስቦታል"

መገናኛ ብዙሃኑን የሚያስተዳድረው የዩናይትድ ስቴትስ ግሎባል ሚዲያ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አማንዳ ቤኔት በበኩላቸው ባወጡት መግለጫ፣ ከርማሺቫ የተከበረች ጋዜጠኛ እና በማህበረሰቧ ተወዳጅ መሆኗን የገለፁ ሲሆን "እስሯ ፍፁም ኢ-ፍትሃዊ በመሆኑ በአስቸኳይ መፈታት አለባት" ብለዋል።

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሲፒጄ እና ድምበር የለሽ የጋዜጠኞች ማህበርም እንዲሁ እስሩን አውግዘዋል።

"ሲፒጄ የአሜሪካ እና ሩሲያ ጥምር ዜግነት ያላት ጋዜጠኛ አልሱ ከርማሺቫ በተሳሳተ የወንጀል ክስ መታሰሯ በእጅጉ አሳስቦታል" ያሉት በሲፒጄ የሩሲያን ጉዳይ የሚከታተሉት ጉሎንዛ "የሩሲያ ባለስልጣናት በአስቸኳይ እንዲለቃት እና በእሷ ላይ የተመሰረቱት ክሶች በሙሉ እንዲቋረጡ" ሲሉ ጠይቀዋል። "ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም። የከርማሺቫ እስር ሩሲያ ነፃ ጋዜጠኝነት ለማፈን ያላት ቁርጠኝነት ያሳያል" ሲሉም አክለዋል።

የድምበር የለሽ ጋዜጠኞች ማህበር፣ የዩናይትድ ስቴትስ ቢሮ ኃላፊ ክሌይተን ዌይመርስ በበኩላቸው "አልሱ ከርማሺቫ፣ ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ የሩሲያ ዓለም አቀፍ የማስፈራራት ዘመቻ ሰለባ ስትሆን ሁለተኛዋ የአሜሪካ ጋዜጠኛ ናት" ብለዋል። ድምበር የለሽ ጋዜጠኞች ማህበር እስሩን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያወግዘውም አስታውቀዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ምላሽ እንዲሰጥ በኢሜል ቢጠየቅም፣ ምላሽ አልሰጠም።

ከርማሺቫ በሩሲያ የታሰረች ሁለተኛ የአሜሪካ ጋዜጠኛ ስትሆን፣ የዎል ስትሪት ጆርናል ዘጋቢ የሆነው ኢቫን ገርኮቪችም ከመጋቢት ወር ጀምሮ ሞስኮ ውስጥ በእስር ላይ ይገኛል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG