በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያዊው ጋዜጠኛ ለጨረታ ያቀረበው የኖቤል ሽልማት ሜዳይ 103.5 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ


ዲሚትሪ ሙራቶቭ
ዲሚትሪ ሙራቶቭ

ከሩሲያ የመጨረሻዎቹ ነፃ ጋዜጦች የአንዱ ዋና አዘጋጅ የነበረው ዲሚትሪ ሙራቶቭ እአአ በ2021 የተቀበለው የኖቤል የሰላም ሽልማት አካል የሆነውን ሜዳይ በጦርነቱ ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉትን የዩክሬን ህፃናት ለመርዳት በያዘው ዕቅድ መሰረት ጨረታ ላይ ካዋለው በኋላ ነው ሪከርድ የሰበረ በተባለ ዋጋ በ103 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የተሸጠው።

ጨረታውን ያዘጋጀው ‘Heritage Auctions’ አስተባባሪዎች የጨረታውን አሸናፊ ማንነት ይፋ አላደረጉም። ዕለቱ ትናንት ከታሰበው የስደተኞች ቀን ጋር ተገጣጥሟል።

ከጨረታው ሽያጭ የተገኘው ገንዘብ ተፈናቃዩን የዩክሬን ህፃናት ለመርዳት ጥረት እያደረገ ላለው በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ህፃናት መርጃ ድርጅት/ዩኒሴፍ/ እንደሚሰጥ ተገልጧል።

ሙራቶቭ እና ፊሊፒናዊቱ ጋዜጠኛ ማሪያ ረሳ በየሃገሮቻቸው የንግግር ነፃነት እንዲከበር ላደረጉት ጥረት የ2021ዱ የኖቤል የሰላም ሽልማት የጋራ ተሸላሚዎች መሆናቸው ይታወሳል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2014 በተመሳሳይ ለጨረታ የዋለ የኖቤል ሽልማት ሜዳይ 4.76 ሚሊዮን ዶላር ነበር የተሸጠው።

ሙራቶቭ ትናንት ጨረታው ከተጠናቀቀ በኋላ በሰጠው አስተያየት “ከፍ ያለ የትብብር መንፈስ ይንጸባረቅ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጌ ነበር፤ ሆኖም ግን ይህን ያህል እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አልተበቅኩም ነበር” ብሏል።

XS
SM
MD
LG