በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ላቭሮቭ ምዕራቡ ዓለም በዩክሬን “የዘር ማጥፋትን እየደገፈ ነው” አሉ


የብሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልበርት ሺንጊሮ፣ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቫሮቭ
የብሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልበርት ሺንጊሮ፣ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቫሮቭ

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቫሮቭ፣ የምዕራቡ ዓለም፣ ለፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለነስኪ “የሰላም ዕቅድ” በሚሰጠው ድጋፍ፣ ዩክሬን ውስጥ፣ “የዘር ማጥፋትን እየደገፈ ነው፤” ሲሉ፣ ትላንት ማክሰኞ፣ ብሩንዲ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናገሩ፡፡

ላቭሮቭ፣ እ.ኤ.አ. ግንቦት 31፣ ቡጅንቡራ ውስጥ ከብሩንዲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልበርት ሺንጊሮ ጋራ በሰጡት መግለጫ፣ የዩክሬኑ “የሰላም ዕቅድ”፣ በምሥራቅ ዩክሬንና ክራይሚያ ውስጥ፣ “የሩሲያ የኾነውን ሁሉንም ነገር እያወደመ ነው፤” ብለዋል፡፡ ላቭሮቭ ይህን ስላሉበት ምክንያት አስረጅ አልጠቀሱም፡፡

ይኹን እንጂ ሩሲያ፣ ምዕራቡ ዓለም፥ በምሥራቅ ዶናባስ ግዛት እና በሌሎች አካባቢዎች፣ የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ በኾኑ ዩክሬናውያን ላይ ስለሚፈጸመው ግድያ ችላ ይላል፤ የሚል ክሥ፣ ለረጅም ጊዜ ስታሰማ መቆየቷን፣ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የዜለነስኪ “የሰላም ዕቅድ”፥ የሩሲያ ጦር፣ እ.ኤ.አ. በ2014፣ ሞስኮ በኃይል ወደ ራሷ የቀላቀለቻትን ክራይሚያን ጨምሮ፣ ከሁሉም የዩክሬን ግዛቶች ለቆ እንዲወጣ የሚሻ ነው፡፡

ብሩንዲ የሚገኙት ላቭሮቭ፣ በተያዘው ዓመት፣ ቢያንስ አፍሪካን ሦስት ጊዜ ያህል መጎብኘታቸው ተነግሯል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ፣ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሞትሮ ኩሌባም፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሩዋንዳንና ሞዛቢክን የጎበኙት፣ ባለፈው ሳምንት እንደነበር፣ በሮይተርስ ዘገባ ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG