በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የህወሓት ታጣቂዎች በሱዳኑ ጦርነት ተሳትፈዋል መባላቸውን የትግራይ ክልል አወገዘ


ፎቶ ፋይል፦ ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ
ፎቶ ፋይል፦ ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ

የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኀይሎች ቡድን፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ አሠቃቂ ድርጊቶችን ፈጽመዋል በሚል ክስ የሚቀርብባቸው” ያላቸው የህወሓት ኀይሎች፣ ከሱዳኑ ጦር ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ መኾናቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ መሰብሰቡን አስታውቋል።

በጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው ኀይል፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በኤክስ ማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ ቀደም ሲል፣ የሱዳን ጦር የውጪ ተዋጊዎችን እንደሚቀጥር ገልጾ ዓለም አቀፍ ብዙኀን መገናኛዎች የዘገቡትን ዜና እንደሚያረጋግጥ አመልክቷል።

“ጦርነቱ እ.አ.አ. ሚያዚያ 15 ቀን 2023 ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ፣ የሱዳን ጦር የልዩ ልዩ ሀገራት የውጭ ተዋጊዎችንና ቡድኖችን ርዳታ ጠይቋል፤” ያለው የፈጥኖ ደራሽ ቡድኑ መግለጫ፣ “የውጭ ኀይሎች” ሲል የጠቀሳቸው ቡድኖች አየር ኀይሉን በመደገፍ፣ በምሕንድስና፣ መድፎችን በማንቀሳቀስ፣ ወታደራዊ ድሮኖችን በማሰማራት፣ የመረጃ ጦርነትን በማካሔድና በመሳሰሉት ተግባራት የሱዳንን ጦር ይደግፋሉ፤ ሲል ከሷል። በውጊያ ወቅት የተገደሉ በርካታ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን መመዝገቡንም ጠቅሷል።

ክሱን ተከትሎ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፣ የፈጥኖ ደራሹን መግለጫ “መሠረት የሌለው” ሲል አጣጥሏል፤ የፈጥኖ ደራሹንም ክስ አጥብቆ እንደሚያወግዘውና በከፍተኛ ኹኔታም እንደሚቃወመው ገልጿል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚኹ መግለጫው፣ የፈጥኖ ደራሹ ኀይል ውንጀላ፥ በሱዳኑ ጦር ላይ ለሚያደርገው ዘመቻ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማሰባሰብ የተነደፈ ሊኾን እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት በአሳዛኝ ኹኔታ መቅጠፉን በገለጸው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ "የህወሓት ተዋጊዎች ተሳትፈዋል የሚለው ውንጀላ በምናባዊ ፈጠራ ላይ የተመሠረተ ነው፤" ብሏል።

አስተዳደሩ አክሎ፣ ህወሓት የፖለቲካ ድርጅት መኾኑንና የታጠቀ ክንፍ ወይም የተደራጀ ሚሊሺያ እንደሌለው ገልጿል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሔደው ጦርነት በርካታ የትግራይ ተወላጆች ወደ ሱዳን በተሰደዱበት ወቅት፣ ጥገኝነት በሰጠችው ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት ምንም ምክንያት እንደሌለው አመልክቷል።

ሁለቱም የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች፣ ግጭቱን የሚያባብሱ መግለጫዎችን ከማውጣት እንዲቆጠቡ ያሳሰበው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ፣ ይልቁንም ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማምጣት በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እንዲወያዩ ጠይቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG