የሶማሌላንድ ስደተኞችን፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ወደተዘጋጀላቸው ዐዲስ የመጠለያ ማዕከል ማዛወር ተጀመረ፡፡
በሶማሌላንድ በተቀሰቀሰ ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ ለገቡ ሶማልያውያን ስደተኞች፣ በሶማሌ ክልል ዐዲስ የመጠለያ ማዕከል መዘጋጀቱን፣ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት አስታወቀ፡፡
በሶማሌ ክልል በቡክ ወረዳ ሚርቃን በተባለ አካባቢ፣ ለማዕከልነት በተለየው በ60 ሄክታር መሬት ላይ፣ ከድንኳንና ከሌሎችም ቁሳቁሶች የስደተኞች መጠለያዎች እየተገነቡ እንደኾነና እስከ አኹን ድረስ 2ሺሕ500 ስደተኞች ወደ ዐዲሱ ጣቢያ መጓጓዛቸውን፣ የተቋሙ ኮምዩኒኬሽንስ የውጭ ግንኙነት ዲሬክተር፣ አቶ በአካል ንጉሤ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡
የዐዲሱ መጠለያ ማዕከል መዘጋጀት፣ የስደተኞቹን የርዳታ እና የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) በአወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በዐዲሱ የሚርቃን መጠለያ ማዕከል፣ ስደተኞቹ ከነዋሪው ማኅበረሰብ ጋራ መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንደሚጋሩም፣ አቶ በአካል ተናግረዋል፡፡
በሶማሊላንድ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት፣ ላስአኖድ ከተባለው አካባቢ፣ እስከ አሁን ድረስ፣ 100 ሺሕ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ያስታወቁት አቶ በአካል፣ ርዳታ ማግኘት የቻሉት ግን፣ 57ሺሕ የሚኾኑቱ ብቻ ናቸው፤ ብለዋል፡፡ በመኾኑም፣ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ፣ ለስደተኞቹ ተጨማሪ ድጋፍ የሚውል የርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ዲሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።