በአዲስ አበባ የሚገኘው የዩናትድ ስቴይትስ ኢምባሲ በሚቀጥለው አመት የሚከበረውን የፕሬዝደንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልት “የአራቱ ነጻነቶች” ንግግር አስመልክቶ የጥበብ ውድድር አዘጋጅቷል።
የፕሬዝደንቱ ንግግር የመሰጠው አሜሪካዊ ሰአሊ ኖርማን ሮክዌል በ1935 ዓ.ም “የአሜሪካ ኑሮ” በሚል አራት የስእል ራብአይ ለትእይንት አብቅቷል። እነዚህ ታዋቂ ስእሎች በዚህ በዋሽንግተን ዲሲ እየታዩ ይገኛሉ።
በዋሽንግተን ዲሲ እምብርት የሚገኘው የስሚትሶኒያን ማእከል የታዋቂውን አሜሪካዊ ሰአሊ ኖርማን ሮክዌል ስራዎች ለትእይንት አቅርቧል።
“የአሜሪካ ኑሮ” በሚል የተሳሉት አራቱ ስእሎች በፕሬዝደንቱ “የአራቱ ነጻነቶች” ንግግር የተቃኙ ናቸው። የሃይማኖት ነጻነት፣ የመፈልግ ነጻነት፣ ከፍራቻ ነጻ መሆንና የመናገር ነጻነት ናቸው አራቱ ነጻነቶች።
አንደኛው ስእል በህዝብ መካከል አንድ ሰው ተነስቶ ሲናገር ያሳያል። ሰዎች ተሰባስበው ሲጸልዩ፣ ቤተሰቦች በምግብ በተሞላ የምግብ ገበታ ላይ ተቀምጠውና ባልና ሚስት ልጆቻቸውን ሲያስተኙ የሚያሳዩ ናቸው ስእሎቹ።
አዲስ አበባ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴይትስ ኢምባሲ የፕሬዝደንት ሩዝቬልት ንግግር የተደረገበትን 70ኛ አመት በሚቀጥለው አመት መከበሩን አስመልክቶ ነው ይሄንን የስእል ውድድር የሚያካሂደው።
በኤግዚቢሽኑ ከቀረቡት የኖርማን ሮክዌል ስራዎች በርካታዎቹ በአሜሪካዊው ፊልም ሰሪ ጆርጅ ሉካስ ባለቤትነት ያሉ ናቸው።
“ስለእውነተኛ በየለቱ የምናያቸው ሰዎች ነው የሚያወራው በፍሬም ውስጥ የሚያሳየን” ይላላ ጆርጅ ሉካስ “ይሄንን ችሎታውን አደንቅለታለሁ።”
ታዋቂው የፊልም ሰሪ ስቲቨን ስፒልበርግም የኖርማን ሮክዌል አድናቂ ነው። ይህወትን በሲኒማ እንደምናሳየው ሮክዌል በእርሳስ በሚሞነጫጭራቸውና በዘይት ቀለም በሚስላቸው ስራዎቹ ኑሮን ቅልብጭ አድርጎ ያሳያል ይላል። በተለይ አሜሪካዊያኑን ኑሮ።
ፕሬዝደንት ሩዝቬልትና ሰአሊው ኖርማን ሮክዌል ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ነበራቸው። አጼ ሃይለ-ስላሴ በ1935ዓም ለፕሬዝደንት ሩዝቬልት አሁን በሽሮሜዳ የሚገኘውን የአሜሪካ ኢምባሲ እንዲሰራ መሬቱን ሰጥተዋል።
ሰአሊው ሞርማን ሮክዌል ወደ ኢትዮጵያ በ1945ዓም ተጉዞ ነበር። በዚያን ጊዜ በሰላም ጓድነት ይሰሩ የነበሩ አሜሪካዊያንን ስራ በቡርሹ ለማስቀረት ነበር ሮክዌል ወደ ኢትዮጵያ ያቀናው።
በደሴ ከተማ አቅራቢያ አንድ አሜሪካዊ የሰላም ጓድ የቤተሰቡ አካል ሆኖ በሚኖርበት መንደር እርሻ ከሚያርስ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ጋር ሆኖ የሳለው ስእል ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ስራው ነው። ወደ ኋላ ስእሉ በዩናይትድ ስቴይትስ የፖስታ ድርጅት ቴምብር ሆኖ ወጥቷል።
ያሜሪካ ኢምባሲ ለዚህ ውድድር የ25ሽህ ብር ሽልማት አዘጋጅቷል። የማመልከቻ ቀኑ የሚያልፈው በአውሮፓዊያኑ አመት 2010 የመጨረሻ ቀን ዲሴምበር 31 ቀን ነው።