በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ወደ ዓረብ አገራት የሚፈልሱ ሴቶችና ሕጻናት ቁጥር እየጨመረ ነው - አይኦኤም


የአይኦኤም ኃላፊ አንቶኒዮ ቪቶሪኖ
የአይኦኤም ኃላፊ አንቶኒዮ ቪቶሪኖ

በየመን አቋርጠው ወደ ዓረብ አገራት የሚገቡ ሕጻናትና ሴቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩንና ይህም አሳሳቢ መሆኑን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) አስታውቋል፡፡

ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ጂቡቲ በመነሳት የሚደረገው እጅግ አስቸጋሪ ጉዞ ወይም ምሥራቃዊ የፍልሰት መሥመር በመባል በሚታወቀው መንገድ የሚደረገው ፍልሰት ባለፈው ዓመት 64 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ከነልጆቻቸው እንዲሁም ልጆች ብቻቸውን የተሻለ ሕይወት ፍለጋ አደገኛውን ጉዞ እንደሚያደርጉ የአይኦኤም ኃላፊ አንቶኒዮ ቪቶሪኖ ለአሶስዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ለፍልሰቱ መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉን ኃላፊው ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በፊት ሴቶችና ሕጻናት አደገኛውን የበረሃ ጉዞ እንደማይሞክሩት የገለጹት ኃላፊው ፍልሰተኞቹ በመንገዳቸው ላይ ለወሮበሎች፣ ለሕገ ወጥ አስተላላፊዎች፣ ለአስገድዶ መደፈርና ሁከት እንደሚጋለጡ፣ ወደ የመን ለሚያመሩ 1 ሚሊዮን ፍልሰተኞች የሚያስፈልገውን 84 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለመጠየቅ ናይሮቢ የተገኙት ኃላፊው አንቶኒዮ ቪቶሪኖ ተናግረዋል፡፡

በመንገድ ላይ ስለሚገጥማቸው አደጋና በየመን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ፍልሰተኞቹ እንደማያውቁና አንድ ግዜ መንገድ ላይ ከገቡ ግን አይኦኤም መሠረታዊ የጤና ግልጋሎት እንደሚሰጥ አንዳንዴም ወደ መጡበት አገራት እንደሚመልስ ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።

አይኦኤም ባለፈው ዓመት 2ሺህ 700 ፍልሰተኞችን ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን የአሶስዬትድ ፕረስ ሪፖርት አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG