የግብጽ ባለሥልጣናት በውጭ ለሚኖሩ ከሃያ በላይ ለሚሆኑ ጋዜጠኞች፣ ተችዎችና የህግ ጠበቆች ፓስፖርት፣ የልደት ምስክር ወረቀትና ሌሎች ሰነዶችን ለመሰጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተመልካች ቡድን ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የግብጽ መንግሥት በተለያዩ ስድስት አገራት የሚኖሩ ግብጻውያንን አስፈላጊ ሰነዶች የማግኘት ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን የገለጸው ቡድኑ “የግብጽ መንግሥት “በውጭ የሚኖሩትን ለመቅጣትና ዝም ለማሰኘት የሚያደርገውን ጥረት እያጠናከረ ነው” ብሏል፡፡
መሠረቱን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ሂዩማን ራይት ዎች ሰነዶቻቸውን የተከለከሉ መሆናቸውን የተናገሩ በውጭ አገር የሚኖሩ 26 ግብጻውያንን ማነጋገሩን ገልጾ ከእነዚህ መካከል ተቃዋሚዎችን ጨምሮ፣ ጋዜጠኞችና የህግ ባለሙያዎች እንደሚገኙበት አስታውቋል፡፡
እኤአ በ2014 የግብጹ የፕሬዚዳንት አብዱል ፋታ አል ሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ መንግሥታቸው በተቃዋሚዎች ላይ የሚያካሂደውን መጠነ ሰፊ እምርጃ የቀጠለ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን ማሰሩ ተዘግቧል፡፡
ስለ ጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የግብጽ ባለሥልጣናት መልስ አለመስጠታቸውን የአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡