በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን በዜጎች ላይ ለተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች የሰብአዊ መብት ተሟጋቶች የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉን በተለይ ተጠያቂ አደረጉ


ፎቶ ፋይል፦ በሱዳን ዳርፉር ያለውን ግጭት ሸሽተው በሱዳን እና በቻድ መካከል ያለውን ድንበር በእግራቸው በማቋረጥ የቻድ መጠለያ ጣቢያ የሚደርሱ ሱዳናውያን እአአ ነሐሴ 4/2023
ፎቶ ፋይል፦ በሱዳን ዳርፉር ያለውን ግጭት ሸሽተው በሱዳን እና በቻድ መካከል ያለውን ድንበር በእግራቸው በማቋረጥ የቻድ መጠለያ ጣቢያ የሚደርሱ ሱዳናውያን እአአ ነሐሴ 4/2023

አንድ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሞያዎች በየበኩላቸው ባወጧቸው መግለጫዎች፡ ሁከት ባልተለየው የምዕራብ ዳርፉር ግዛት ‘ፈጽሟል’ ባሏቸው በሴቶች ላይ የተነጣጠሩ ጥቃቶች በተለይ የሱዳኑን ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ወነጀሉ።

በሃገሪቱ ጦር እና በተቀናቃኙ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል መካከል በተቀሰቀሰው እና አምስተኛ ወሩን በያዘው ግጭት፡ ቡድኑ አረብ ያልሆኑ ዜጎች በሚኖሩበት የምዕራብ ዳርፉር ክልል በሴቶች እና ልጃገረዶች፤ እንዲሁም በማሕበረሰብ አንቂዎች ላይ የተነጣጠሩ ጥቃቶችን መፈጸሙን ዋና መቀመጫውን በኒው ዮርክ ያደረገው ሂዩማን ራይትስ ዎች በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል።

የመብቶች ተሟጋቹ ቡድኑ አክሎም ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ካለፈው የሚያዝያ ወር አጋማሽ አንስቶ እስከ ሰኔ ወር አጋማሽ በነበረው ጊዜ ውስጥ ቁጥራቸው 78 በሚደርሱ ሴቶች እና ልጃ ገረዶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች መፈ’ጸሙን መመዝገቡን አመልክቷል።

ልዩ ኃይሉ እና አጋር ሚልሻዎች በተለይ የአረብ ዝርያ በሌላቸው የአፍሪካውያን ማሕብረሰብ አባላት ላይ በተነጣጠረ ጥቃታቸው በዳርፉር እየተካሄደ ያለው ውጊያ የጎሳ መልክ እየያዘ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት ባለፈው የሰኔ ወር ባወጡት መግለጫ ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል።

"ጃንጃዊድ" በመባል የሚታወቁት በሱዳን መንግስት የሚደገፉ የአረብ ሚልሻዎች እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በፈጸሙት መጠነ ሰፊ ግድያ፣ የአስገድዶ መድፈር እና ሌሎች አሰቃቂ ድርጊቶች ሲከሰሱ፤ ዳርፉር የዘር ማጽዳት ወንጀል የተፈጸመባት ግዛት ሆና መቆየቷም አይዘነጋም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG