የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና የተቃዋሚዎቹ መሪ ሪያክ ማቻር ትናንት ቅዳሜ ይመሠርቱታል ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን የአንድነት ሽግግር መንግሥት ሳይመሠርቱ ቀርተዋል፡፡
የዚህ መንግሥት ምሥረታ ወገኖቹ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ ደርሰውት የነበረ ስምምነት ቁልፍ አንጓ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የተቃዋሚው የሱዳን ሕዝብ አርነት ንቅናቄ መሪ ሪያክ ማቻር የመንግሥቱ አባላት የሚሆኑ ዕጩ ሚኒስትሮችን ስም ዝርዝር ሳይልኩ መቅረታቸው ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ “ሳልቫ ኪር ስምምነቱን በሚጥስ መንገድ ሃያ ስምንት ስቴቶችን ወይም ክልላዊ መንግሥታትን ፈጥረዋል” ሲሉ ተቃዋሚዎቹ ከስሰዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቃዋሚዎቹ መሪ ዶ/ር ሪያክ ማቻር እንደ ባላንጣ ሲተያዩ ከቆዩት ከዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ለመወያየት ማምሻውን ወደ ካምፓላ በርረዋል፡፡
ማቻር ወደ ዩጋንዳ ሲሄዱ የደቡብ ሱዳኑ ግጭት ከተጫረ ወዲህ ላለፉ ሁለት ዓመታት የመጀመሪያቸው መሆኑ ነው፡፡
ማቻር በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤታቸው ለጉዟቸው ከመነሣታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡
መግለጫውን የተከታተለው እስክንድር ፍሬው ለቪኦኤ የዘገበውን ከላይ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡