በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ የሰሞኑ የመብቶች ድርጅቶች ሪፖርት እንደሚያሳስባት ዩናይትድ ስቴትስ አስታወቀች


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት

አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ህዩመን ራይትስ ዋች ሰሞኑን በጋራ ባወጡት ሪፖርት ላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ “በአማራ ባለሥልጣናት ምዕራብ ትግራይ ውስጥ እየተፈፀመ ነው” ያለው የጎሣ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጭካኔ አድራጎት በብርቱ እንደሚያሳስበው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በተለይ አድራጎቶቹ “ዘር ማፅዳት” ተብለው የሚፈረጁ ሆነው መገኘታቸው ዩናይትድ ስቴትስን በጥልቅ እንደሚረብሽ በመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ስም የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በሺሆች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያዊያን ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ለህይወት አስጊ በሆኑ ሁኔታዎች በዘፈቀደ ታስረው የሚገኙ መሆናቸው መዘገቡ ትኩረታቸውን አበርትቶ የሳበ መሆኑን ቃል አቀባዩ ጠቁመው ታስረው የሚገኙ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በሙሉ በአፋጣኝ እንዲለቀቁና እሥር ቤቶቹን ሁሉ ዓለምአቀፍ ቃኚዎች ማየት እንዲችሉ ባለሥልጣናቱ ፈቃድ እንዲሰጡ ሃገራቸው ጥሪ እንደምታስተላልፍ ገልፀዋል።

ለቀውሱ ዘላቂ መፍትኄ ለማስገኘት የሚደረገው ጥረት አካል በሆነ ሁኔታ በቀውሱ ውስጥ ተሣታፊ በሆኑት ሁሉም ወገኖች በተፈፀሙ የጭካኔ አድራጎቶች ላይ ተዓማኒ ምርመራ መካሄዱና ፈፃሚዎቹ እንዲጠየቁ ማድረግ አሁንም የሃገራቸው ፅኑ አቋም መሆኑን ኔድ ፕራይስ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከመንግሥታቱ ድርጅት ኮሚሽን ባለሙያዎች ጋር እንዲተባበርም ሃገራቸው ጥሪ እንደምታደርግ ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል።

የጭካኔ አድራጎቶች እየተፈፀሙ መሆናቸውን የሚናገሩት ሪፖርቶች መቀጠል ወታደራዊው ግጭት በአፋጣኝ መቆም ያለበት መሆኑን በአፅንዖት እንደሚያስገነዝቡ የሚያመለክተው ይኸው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መግለጫ “በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ ባለሥልጣናት የታወጀውን ፀብን የማቆም ውሣኔ በብርቱ እንደግፋለን” ብሏል።

“እርምጃው ህይወት አድኑ ድጋፍ እንዲደርስ የመጀመሪያዎቹ አቅርቦቶች በመድረሳቸው መታጀቡን የሚናገሩት ዜናዎች አስደስተውናል” ይላል የቃል አቀባዩ መግለጫ።

“ሁሉም የታጠቁ ተሣታፊዎች በሲቪሎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችንና ሁከቶችን እንዲያወግዙና እንዲያቆሙ፣ ሁሉም የውጭ ኃይሎች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ፣ አካባቢያዊ ባለሥልጣናት ሁሉ የፀጥታ ኃይሎቻቸውን ከአጎራባች ክልሎች ግዛቶች እንዲመልሱ ዩናይትድ ስቴትስ ጥሪያዋን በድጋሚ ታስተላለፋለች” ብለዋል ፕራይስ።

ፀብ የማቆሙ ውሣኔ፣ ያልተገደበና የማያቋርጥ ሰብዓዊ አቅርቦት መኖሩን፣ በሁሉም ወገኖች በተፈፀሙ የመብቶች ጥሰቶችና ረገጣዎች ላይ ግልፅ ምርመራ መካሄዱን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ግጭት በድርድር ላይ የተመሠረተ መፍትኄ መገኘቱን ሁሉም ወገኖች እንዲያረጋግጡ ዩናይትድ ስቴትስ ጥሪዋን ማሰማቷን እንደምትቀጥል ይኸው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ቃል አቀባይ ያወጡት መግለጫ አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG