ዋሺንግተን ዲሲ —
ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩት ዓመት ውስጥ በመላው ዓለም 53 ጋዜጠኞች መገደላቸውን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማኅበር ባወጣው የዓመቱ ማጠቃለያ ሪፖርት ገለፀ። በ2020 ዓ.ም ከተገደሉት ጋዜጠኞች ውስጥ 84 በመቶ የሚሆኑት ሆን ተብለው በተፈፀሙ ጥቃቶች መገደላቸውን የሚገልፀው የድርጅቱ ሪፖርት፤ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች የተገደሉት በሜክሲኮ ነው ብሏል።
በከፍተኛ ቁጥር ጋዜጠኞች የተገደሉባቸውን አምስት አገራት ሲዘረዝርም ሜክሲኮ ስምንት፣ ኢራቅ ስድስት፣ አፍካጋኒስታን አምስት እንዲሁም በፓኪስታን እና በህንድ አራት፣ አራት ጋዜጠኞች ተገድለዋል።
በሃገር ውስጥ የሙስና ጉዳዮች ላይ የምርመራ ሪፖርቶችን በመሥራታቸው እና በማጠናቀር ላይ እያሉ በዚህ ዓምተ ዐስር ጋዜጠኞች ተገድለዋል። የወንጀል ጉዳዮችን ለማጋለጥ ሲሰሩ የነበሩ አራት ጋዜጠኞች እንዲሁም የተቃውሞ እንቅስቃሴን በመዘገብ ላይ የነበሩ ሰባት ጋዜጠኞች የተገደሉበት ዓመት ነው ብሏል ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት።