ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እያለ ወደ አዋሽ ከተማ ሲቃረብ ሐዲዱን ስቶ በመገልበጥ ቁጥሩ ከ418 የሚበልጥ ሕይወት የጠፋበት የባቡር አደጋ የደረሰው ከአርባ ዓመታት በፊት በ1977 ዓ.ም. በዛሬው ዕለት ነበር፡፡ የፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ የባቡር መስመር ኩባኒያን ጠቅሶ አሶሲየትድ ፕሬስ በዕለቱ ያስነበበው ዘገባ እንዳተተው በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ 559 ሰዎች ቆስለዋል፡፡
1 ሺሕ የሚኾኑ መንገደኞችን በሰባት ፉርጎዎች አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው ባቡር አዋሽ ድልድይ ላይ በፍጥነት እየበረረ ደርሶ ተጠምዝዞ ለማለፍ ሲል ሐዲዱን ስቶ ሸለቆው ውስጥ በመገልበጡ መኾኑን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ የባቡር ኩባኒያውን እና የርዳታ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ አሶሲየትድ ፕሬስ በዕለቱ የወጣው ዘገባ ያትታል፡፡ በወቅቱ የደረሰው አደጋም ፣ ለረሀብ ተጎጂዎች የሚውል አቅርቦት ማጓጓዝ ላይም ከባድ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት መናገራቸውን ዘገባው አያያዞ ጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በአፍሪካ አህጉርም ኾነ በዓለም ላይ ከደረሱ እጅግ ከባድ እና ዘግናኝ የባቡር አደጋዎች መካከል አንዱ የኾነው ይህ አደጋ በታሪክ " የአዋሹ የባቡር አደጋ" እየተባለ ይታወሳል፡፡
መድረክ / ፎረም