በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሁቲ አማፂያን በአንድ መርከብ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ


በቀይ ባሕር ላይ ትጓዝ በነበረች አንድ መርከብ ላይ ማምሻውን ተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘሩን በተመለከተ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የእንግሊዝ የባሕር መጓጓዣና ንግድ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከጀመረ ወዲህ፣ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የሁቲ አማፂያን፣ በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት በመቃወም እና ከፍልስጤምውያን ጋራ ያላቸውን አንድነት ለማሳየት በሚል፣ በቀይ ባሕር ላይ የሚመላለሱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ሰንብተዋል።

ከየመን 174 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በአንድ መርከብ አቅራቢያ ፍንዳታዎች መከሰታቸውን አንድ ጀልባም መርከቡን ተጠግቶ እንደነበር ካፕቴኑ ሪፖርት ማድረጋቸው ታውቋል።

ጥቃቱ ሦስት ጊዜ መፈጸሙንና ቦምብ ተሸካሚ የድሮን ጀልባዎች ጥቅም ላይ እንደዋሉ የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፂያን ጥቃት የመጣው፣ የሐማስ ባለሥልጣን እስማኤል ሃኒየህ ቴህራን ውስጥ መገደሉን ተከትሎ፣ ኢራን የበቀል ጥቃት ለመውሰድ ተዘጋጅታለች በሚባልበት ወቅት ነው።

የሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር ላይ እያደረሱ ያለው ጥቃት፣ በዓመት 1 ትሪሊየን ዶላር ግምት ያለው ሸቀጥ የሚተላለፍበትን እና እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅን እና አውሮፓን በንግድ የሚያስተሳስረውን መተላለፊያ አስተጓጉሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG