በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጥቃት ምክንያት በቀይ ባህር የሚጓጓዙ እቃዎች በሠላሣ ከመቶ ቀንሷል - አይ ኤም ኤፍ


የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF)
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF)

የየመን ሁቲ አማፂያን በቀይ ባህር ላይ የሚያደርሱት ጥቃት መጨመሩን ተከትሎ፣ በቀይ ባህር ላይ የሚጓጓዙ እቃዎች መጠን በአንድ ሦስተኛ መቀነሱን፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ረቡዕ እለት አስታውቋል።

የአይ ኤም ኤፍ የመካከለኛው ምስራቅ እና መካከለኛው እስያ ዳይሬክተር ጂሃድ አዙር "እቃ ማጓጓዝ በ30 ከመቶ ቀንሷል" ያሉ ሲሆን በተለይ የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ከገባ ወዲህ የንግዱ መቀዛቀዝ መባባሱን አመልክተዋል።

በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች፣ እ.አ.አ ከህዳር 19 ወዲህ በንግድ እና የባህር ኃይል መርከቦች ላይ ከሠላሣ በላይ ጥቃቶች ማድረሳቸውን፣ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር (ፔንታገን) ማክሰኞ እለት አስታውቋል። አማፅያኑ ጥቃቶቹን የሚያካሂዱት ለፍልስጤም አጋርነታቸውን ለማሳየት እና ከጥቅምት ወር ወዲህ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት ለመቃወም መሆኑን አስታውቀዋል።

በዓለም በጣም ብዙ መርከቦችን በማስተላለፍ የሚታወቀው የስዊዝ ካናል በኩል የሚጓጓዙ እቃዎች መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ37 ከመቶ መቀነሱን የአይ ኤም ኤፍ መረጃ ያሳያል። ካናሉ ቀይ ባህርን ከሜዲትራኒያን ባህር ጋር የሚያገናኝ መስመር ነው።

ዓለም አቀፉ የመርከብ ማጓጓዣ ምክርቤት መረጃ እንደሚያሳየው፣ የሁቲ ጥቃቶች አንዳንድ የመርከብ ኩባንያዎች ቀይ ባህርን እንዲሸሹ እና በደቡብ አፍሪካ በኩል ዞረው እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል።

ቀይ ባህር በተለይ ለአውሮፓ ንግድ ወሳኝ መተላለፊያ ሲሆን፣ በቀይ ባህር ላይ የሚተላለፉ መርከቦችን ደህንነት ለመጠበቅ የተቋቋመውን ጥምረት የምትመራው ዩናይትድ ስቴትስ ሁቲን 'ሽብርተኛ ቡድን' አርጋ በመፈረጅ ዲፕሎማሲያዊ እና የገንዘብ ጫናዎችን ለማድረግ እየጣረች ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ እና እንግሊዝ በየመን የሚገኙትን ሁቲዎች አቅም ለማዳከም ተደጋጋሚ ጥቃት ቢሰነዝሩም፣ በኢራን የሚደገፈው እንቅስቃሴ ግን አሁንም መረከቦች ላይ ጥቃት ማድረሱን ቀጥሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG