ዛሬ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ሁለት የተለያየ ይዘትና ባሕርይ ያላቸው ሰልፎች በኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን ተካሂደዋል፡፡
አንደኛው ሰልፍ በዋይት ኃውስ ቤተመንግሥትና በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፊት ለፊት የተካሄደ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኙት የቻይናና የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ደጅ የተደረገ ነው፡፡
በዋይት ኃውስ ቤተመንግሥትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተደረገው ሠልፍ የኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት እንዲከበርና ለግብፅ ውትወታ የኦባማ አስተዳደር ጆሮ እንዳይሰጥ የሚጠይቅ፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ጥረትም የሚደግፍ ነው፡፡
በቻይናና በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ደጅ የተደረገው ሰልፍ ደግሞ ቻይና ሠልፈኞቹ አምባገነን ላሉት የኢትዮጵያ መንግሥት የምታደርገውን ትብብር እንድታቆም የሚጠይቅና ቻይና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ወዳጅነት የምትፈልግ ከሆነ ከሕዝቡ ጎን ትቁም የሚል ነው፡፡