በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢራቁ ምርጫ ያሸነፉት የሺአ መሪ የኢራንን ተፅእኖ ሊሰብሩ ይችላሉ ተባለ


የኢራቅ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፓርላማ ምርጫውን ውጤት ካፀደቀ በኋላ ነዋሪዎች ደስታቸውን ሲገልጹ
የኢራቅ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፓርላማ ምርጫውን ውጤት ካፀደቀ በኋላ ነዋሪዎች ደስታቸውን ሲገልጹ

በኢራቅ ባለፈው ጥቅምት የተደረገው የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ውጤት ተሻሽሎ እንዲጸድቅ በመደረጉ አሸናፊዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጭውን መንግሥት ለመመስረት ድርድር እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በፓርቲዎቹ መካከል ያለው ልዩነት የሀሳብ ሳይሆን፣ በጠባብ የፖለቲ ሥልጣን ፍላጎት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ቀጣዩ የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆናል? የሚለው ጥያቄ ተከታዩ ፈተና መሆኑን ባለሙያዎች ለአሜሪካ ድምጽ ተናገረዋል፡፡

በምርጫው ያሸነፉት የኢራቅ ብሄርተኛው የሺአ ሃይማኖት መሪ ሙቅታዳ አል ሳዳር፣ ኢራን በኢራቅ ላይ ያላትን ተፅእኖ ይሰብራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

ከኦማን በመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ኦስማን አልሻርፊ ለአሜሪካ ድምጽ እንደተናገሩት አልሳዳር የኢራን ደጋፊ ሚሊሻዎችን እንዲፈርሱ የተናገሩ ብቸኛ የፖለቲካ ሰው ናቸው ብለዋል፡፡

የአልሳዳር ቡድን ኢራንን የሚደግፉ ተፎካካሪዎችን በማሸነፍ በምክር ቤቱ 73 መቀመጫዎችን ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡

ይሁን ግን አብላጫውን ድምፅ ባለማሸነፋቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩነትን ስፍራ ለማግኘት የሌሎችን ፖርቲዎች ድጋፍ ማግኘት ያለባቸው መሆኑን ተመልክቷል፡፡

ያን የማያደርጉ ከሆነ፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የኢራቁ ጠቅላይ ሚስትር ሙስጠፋ አል ቃድኺሚ ቦታውን እንደያዙ ሊቀጥሉ ይችላሉ ተብሏል፡፡

አል ቃድኺሚ ወደ ሥልጣን የመጡት እኤአ በ2020 ሲሆን በወቅቱ የኢራንውያን፣ የአሜሪካውያን፣ የሺአ፣ የሱኒ፣ የኩርዶኖችና ሌሎች ድርጅቶችን የተስማማ ድጋፍ በማገኘታቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡

የኢራቅ ጋዜጠኛ ሚና አል ኦራቢ የሳቸው በሥልጣን መቆየት የትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ብሄር የማይወክል በመሆኑ አገሪቱን አረጋግቶ ሊያስቀጥል የሚችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ግን ያን ማድረግ ቀላል ላይሆን እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG