የንግሥት ኤልዛቤት ንግሥና ሰባኛ ዓመት ክብረ በዓል ትናንት ሀሙስ የተጀመረ ሲሆን ዛሬ ከፍተኞቹ የንጉሣዊው ቤተሰብ ከፍተኛ አባላት እና የፖለቲካ ሰዎች የተሳተፉበት የምስጋና ጸሎት ሥነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡ የዘጠና ስድስት ዓመቷ ንግሥት ኤልዛቤት ግን ከመቆም እና ከመራመድ ጋር ተያይዞ አልተገኙም፡፡
ትናንት ለክብረ በዓሉ ከተካሄደው ወታደራዊ ሰልፍ ትዕይንት እና የንጉሣዊ የአየር ኅይል በረራ በኋላ ፊታቸው ላይ ደስታ ይነበባቸው የነበሩት ንግሥት ኤልዛቤት በኪንግሃም ቤተ መንግሥት በረንዳ ላይ ወጥተው የተሰበሰበውን እጃቸውን በማውለብለብ ሰላምታ ሰጥተዋል፡፡
ከዚያም በኋላ ከዊንዘር ቤተ መንግሥት ቤታቸው ሆነው የክብረ በዓሉን ችቦዎች ማብራት ሥነ ስርዐት መርተዋል፡፡ በዛሬው የንግሥናቸው ሰባኛ ዓመት በዓል ሁለተኛ ቀን በቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል የምስጋና ጸሎት ሥነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡
ንግሥት ኤልዛቤት በየጊዜው ከመቆም እና መራመድ ተያይዞ በሚያጋጥማቸው ችግር የተነሳ በቅርብ ጊዚያት በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ሳይገኙ መቅረታቸው ሲታወስ በጸሎት ሥነ ስርዓቱ ላይም ከዊንዘር ቤተ መንግሥት ወደለንደን መጓዝ ስለሚበዛባቸው ቢቀሩ ይሻላል ከሚል ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መደረሱን ከበኪንግሃም ቤተ መንግሥት የወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
የሰልፍ ትርዒቱ እና የአየር ኃይል በረራዎቹን በመጠኑ ምቾት ያልተሰማቸው ቢሆንም ደስ ብሏቸው ተመልክተዋል ብለዋል የቤተ መንግሥቱ ባለሥልጣናት፡፡
ከቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል ሥነ ስርዓት የቀሩት እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሁለተኛው ወንድ ልጃቸው ልዑል አንድሩውም ኮቪድ- 19 ስለያዛቸው እንደማይገኙ ቤተ መንግሥቱ አስታውቋል፡፡