በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ ኦሞ ዞን አንዲት እናት በአንድ ጊዜ አራት ልጆች ወለደች  


በደቡብ ኦሞ ዞን አንዲት እናት በአንድ ጊዜ አራት ልጆች ወለደች
በደቡብ ኦሞ ዞን አንዲት እናት በአንድ ጊዜ አራት ልጆች ወለደች

በደቡብ ኦሞ ዞን ሳላማጎ ወረዳ የአይሎሀ ቀበሌ ነዋሪ የኾነችው ወይዘሮ ማርታ ታከለ በአንድ ጊዜ አራት ልጆችን በሰላም መገላገሏ ተገለጸ፡፡

የወይዘሮ ማርታ ባለቤት አቶ አንጅሎ አዲሱ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጸው የ29 ዓመቷ ባለቤቱ በድንገት ምጥ መጥቶባት ሆስፒታል ከገባች በኋላ ለሰዓታት በምጥ መውለድ ባለመቻሏ በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል በቀዶ ህክምና አራቱንም ልጆች ተገላግላለች።

የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ዳይሬክተር ፣ ዶክተር ቢንያም አስራት፣ ወይዘሮ ማርታ ታከለ ከፀነሰች ከሦስት ወሯ ጀምሮ በሆስፒታሉ የእርግዝና ክትትል ስታደርግ እንደነበረ አመልክተው በእርግዝናዋ ወቅት በውስጥ አካላት መመርመሪያ በአልትራሳውንድ የታየው የሦስት ልጆች ጽንስ ቢሆንም በቀዶ ህክምናው አራት ልጆች እንደወለደች ገልጸዋል፡፡

የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ዳይሬክተር ፣ ዶክተር ቢንያም አስራት፣ ሕጻናቱ ከተወለዱ በኋላ ያነሱትን ፎቶ አጋርተውናል።

ባለቤቱ ቋሚ ሥራ እና ገቢ የሌላት የቤት እመቤት እንደሆነች እና እርሱም ቤተሠቡን የሚያስተዳድረው በጉልበት ሥራ በሚያገኘው የቀን ገቢ መሆኑን የአራት ዓመት ወንድ ልጅ እንዳላቸው የገለጸው አቶ አንጀሎ አሁን ደግሞ “በአንድ ጊዜ የአራት ልጆች አባት መኾኔ ቢያስደስተኝም እንዴት እንደማሳድጋቸው ግራ ገብቶኛል” ሲል ስጋቱን አጋርቷል።

"እስካሁንም የምንኖረው በፈጣሪ ርዳታና እና ባለቤቴ በቀን ሞያተኝነት በምታገኘው ገቢ እየተደጎምን ነው “ ሲል አክሏል።

ሁለት ሴት እና ሁለት ወንድ ሕፃናቱ የተወለዱት ዘጠኝ ወራቸውን ሞልተው እንደኾነም ሐኪሙ አመልክተዋል።

ሦስቱ ሕጻናት ክብደታቸው1 ነጥብ 8 ፣ 1ነጥብ 9፣ እና 1ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ሲኾኑ የአራተኛው ልጅ ክብደት አንድ ኪሎ ብቻ መኾኑን የገለጹት ዶክተር ቢንያም

ለጊዜው ጨቅላ ሕጻናት በሙቀት ማቆያ ውስጥ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ ዛሬ ወደ እናቱ ተመልሷል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ጨቅላ ሕጻናቱም እናታቸውም በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የሕክምና ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከአሁን በፊት በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታሉ አንዲት እናት ሦስት ልጆችን መገላገሏን አስታውሰው በሆስፒታሉ በአንድ ጊዜ አራት ልጆች ሲወለዱ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG