በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ካታር በዓለም ዋንጫው ዝግጅት የሞቱት ሠራተኞች ከ400 እስከ 500 ይሆናሉ አለች


ፎቶ ፋይል - የግንባታ ሠራተኞች በሥራ ላይ ከዶሃ በስተሰሜን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው በአል ባይት ስታዲየም፤ አል ኮሆር፣ ኳታር እአአ 4/29/2019.
ፎቶ ፋይል - የግንባታ ሠራተኞች በሥራ ላይ ከዶሃ በስተሰሜን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው በአል ባይት ስታዲየም፤ አል ኮሆር፣ ኳታር እአአ 4/29/2019.

ለዘንድሮው የዓለም ዋናጫ ዝግጅት መስተንግዶ ዝግጅት ላይ ሲሰሩ ከነበሩ ሠራተኞች መካከል ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውን በዝግጅቱ የተሳተፉ አንድ የካታር ከፍተኛ ባለሥልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ተናገሩ፡፡

የመስተንግዶ ኮሚቴ ዋና ጸሃፊ ሀሳን አልታዋዲ ይህን የተናገሩት ከብሪታኒያው ጋዜጠኛ ፒርስ ሞርጋን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ መሆኑን የአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የተጠቀሰው ቁጥር እስከዛሬ በዶሃ ባለሥልጣናት ከተገለጸው እጅግ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ የመጀመሪያው ነው ለተባለው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ፣ ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ፈጅቷል የተባለውን ስቴዲዮም፣ የባቡር መስመሮች እና ለውድድሩ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት በተሰማሩ ስደተኞች ላይ ምን ያህል ጉዳት ደርሷል የሚለውን የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾችን ጥያቄና ትችት ሊቀሰቅስ እንደሚችልም ተነግሯል፡፡

በሰጡት ቃል መጠይቅ ላይ “የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ትክክለኛው ቁጥር የለኝም ለውይይት በቀረበው ላይ ግን የተጠቀሰው ቁጥር እሱ ነው” ያሉት ባለሥልጣን “የአንድም ሰው ሞት ቢሆን ያው ብዙ ነው፡፡ ግልጽና ቀላል ነው፡፡ ምን ልዩነት ይኖረዋል?” ማለታቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

ዝቅተኛው የሠራተኞች ወርሃዊ ደመወዝ 275 ዶላር እንዲሆን የወሰነችው ኳታር የሠራተኞች ደህንነት የጠበቀ እንዲሆን አዲስ ህግ ማውጣቷ ተነግሯል፡፡

የመብት ተሟጋቾች ግን ካታር ከዚያ በላይ ልታደርግ ይገባታል ብለዋል፡፡

የባለሥልጣኑ አስተያየት በስደተኞች ጉልበት በሚገነቡት በሌሎች የባህረ ሰላጤው አገሮች ትላልቅ ህንጻዎች ላይ የተሰማሩትንም ሠራተኞች ደህንነት በሚመለከት ጥያቄ ማስነሳቱ ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG