ዩናይትድ ስቴትስ ከሩስያ ክሬምሊን ቤተ መንግሥት ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸውን ሁለት መቶ አስር ሰዎች ሃብት እና የፖለቲካ ግንኙነቶቻቸውን በዝርዝር ይፋ ማድረጓ "የጠላት ተግባር ነው" ሲሉ የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ተናገሩ። ሆኖም ሃገራቸው ባፋጣኝ የበቀል ርምጃ ለመውሰድ አትንቀሳቀስም ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግሬስ ሩስያ በአምናው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ በመግባትዋ ለመቅጣት ባለፈው ነሃሴ ወር ባጽደቀው ህግ መሰረት የገንዘብ ሚኒስቴር የመዝገቡን ትናንት ሰኞ ይፋ አድርጉዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ህጉን እያመነቱ መፈረማቸው ሲታወስ ትናንት የአስተዳደራቸው ባለሥልጣናት በክሬምሊን ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል ለጊዜው ዕቅድ እንደሌለ ተናግረዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሄዘር ኑዌርት በጽሁፍ ባወጡት መግለጫ ህጉ ከወዲሁ የሩስያን ኩባኒያዎች እየጎዳ ነው ብለዋል።
በርካታ የሩስያ ባለሥልጣናት በሪፖርቱ የተቆጡ ሲሆን ጠቅላይ ምኒስትር ዲሚትሪ ሜድቬየዴየቭ ”ግንኙነታችንን ለረጅም ጊዜ የሚመርዝ ነው” ብለዋል።
ዛሬ ሞስኮ ውስጥ በአንድ የምረጡኝ ዘመቻ ዝግጅት ላይ ለዘብ ባለ መልኩ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ፑቲን ግን ዝርዝሩ ይፋ መደረጉ ያሳዘነን ቢሆንም ለጊዜው የበቀል ርምጃ ከመውሰድ እንቆጠባለን ብለዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ