በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፑቲን የምዕራባውያንን ተጽዕኖ ለመቋቋም የታለመውን ‘የብሪክስ አባል ሃገራት’ ጉባኤ እያስተናገዱ ነው


 የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ፣ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በካዛን ፣ ሩሲያ፣ እአአ 22/2024
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ፣ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በካዛን ፣ ሩሲያ፣ እአአ 22/2024

የቻይናው ሺ ጂንፒንግ፣ የሕንዱ ናሬንድራ ሞዲ እና ሌሎች የዓለም መሪዎች በቡድኑ ጉባኤ ለመሳተፍ ዛሬ ማክሰኞ ከሩሲያዋ የካዛን ከተማ ገብተዋል።

በርካታ በመልማት ላይ ያሉ አገሮች በአባልነት የሚገኙበት ‘ብሪክስ’ በሩስያ የሚያካሂደውን ይህን ጉባኤ፤ ክሬምሊን በዓለሙ መድረክ ምዕራባውያን ያላቸውን ተጽዕኖ ለመቋቋም በያዘው ጥረት እንደሚያግዘው ተሥፋ ጥሎበታል።

ለሦስት ቀናት የሚዘልቀው ጉባኤ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ በዩክሬን የፈጸሙትን ወራራ ተከትሎ ሞስኮን ለማግለል ዩናይትድ ስቴትስ መሩ ዓለም አቀፍ ጥምረት ተስፋ ያደረገውን ጥረት ያህል እንዳልሰመረለት በጠንካራ ማሳያነት ይጠቀሙበታል ተብሎ ታምኗል።

የክሬምሊን የውጭ ጉዳይ አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ በሰጡት አስተያየት 36 ሃገራት የሚሳተፉበትን እና ከ20 በላይ የሚሆኑት በመሪዎቻቸው የሚወከሉበትን ጉባኤ "ሩስያ ውስጥ ከተካሄዱ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይ ያተኮሩ መድረኮች ሁሉ ግዙፉ" ብለውታል።

ሲመሰረት ብራዚልን፣ ሩሲያን፣ ህንድን፣ ቻይናን እና ደቡብ አፍሪካን ያቀፈው ሕብረት ኢራንን፣ ግብፅን፣ ኢትዮጵያን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን እና ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ በፍጥነት ወደ ገዘፈ ቡድንነት መሸጋገሩ ይታወሳል። ቱርክ፣ አዘርባጃን እና ማሌዢያም በተመሳሳይ አባል ለመሆን በይፋ ሲያመለክቱ፤ ሌሎች ጥቂት አገሮችም ቡድኑን ለመቀላቀል ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል።

ታዛቢዎች ጉባኤውን ሩስያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት ይበልጥ እየተባባሰ በመጣበት በአሁኑ ወቅት፤ ‘የደቡቡ ዓለም ከተባሉት አገራት’ ያላትን ድጋፍ ለማሳየት የያዘችው ጥረት እና ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነቶቿን ለማስፋት የሚረዳ አድርገው ይመለከቱታል።

ከዋናው ጉባዔ በትይዩ 20 ከሚሆኑ አገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ንግግር እንደሚያደርጉ የተገለጸው ፑቲን፤ እስካሁን ከህንዱ መሪ ሞዲ እና ከደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ዘግየት ብሎም ከቻይናው ሺ ጋር ይነጋገራሉ።

ፑቲን ከነገ በስቲያ ሐሙስ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ። ጉቴሬዥ ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ያለውን ጦርነት በተደጋጋሚ መተቸታቸው ይታወቃል። የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሩስያ ሲጎበኙ ያሁኑ የመጀመሪያቸው ይሆናል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG