የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሞቱት የሶቪየት ኅብረት የመጨረሻው ፕሬዚዳንት ሚኻይል ጋርባቾቭ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት እንደማይችሉ የክሬምሊን ቤተመንግሥት አስታወቀ፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬማክሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፑቲን መገኘት የማይችሉት በሥራ ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ጋርባቾቭ የተሟላው ብሔራዊ ሥርዓተ ቀብር የሚፈጸምላቸው ባይሆንም፣ የክብር ዘቦችና እንደዚያባሉ ሥነ ስርዓቶች ላይ የሚሰጡ ሌሎች አገልግሎቶች እንደሚደረጉላቸው ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ፑቲን ዛሬ ማለዳው ላይ ጋርባቾቭ ህክምናቸውን ሲከታተሉ ወደ ቆዩበትና ህይወታቸው ካለፈም በኋላ አስክሬናቸው ወደ ቆየበት ማዕከላዊ የምርምር ሆስፒታል ብቅ ብለው የተሰናበቷቸው መሆኑንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን “በዛሬው ዕለት ይህን ማድረጋቸው፣ እንደለመታደል ሆኖ የፕሬዚዳንቱ የሥራ መርኃ ግብር ቅዳሜ ነሀሴ 28 በሚደረገው ሥርዓት ቀብር ላይ እንዳይገኙ ስለሚከለክላቸው ነው” ብለዋል ዲምትሪ፡፡
የጋርባቾቭ ሴት ልጅ ኧሪና ቪርጋንስካያ (Irina Virganskaya) የአባታቸው ቀብር ቅዳሜ 28፣ ከኒኪታ ክሩቼቭ በቀር ሁሉም የሶቭየት መሪዎች ባረፉበትና ከቤተመንግሥቱ እልፍ ብሎ በሚገኘው በህብረቱ ታሪካዊ ሥፍራ እንደሚፈጸም አስታውቀዋል፡፡