በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፑቲን ዛሬ ቴህራን ናቸው


የዩክሬን ገበሬ ሰብል ሲሰበስብ እና ከበስተጀርባው በርቀት የሚታየው ጭስ በአካባቢው እየተደረገ ያለውን ኃይለኛ ጦርነት ያሳያ፤ በዲኒፕሮፔትሮቭስክ፣ ዩክሬን እአአ ሐምሌ 4/2022
የዩክሬን ገበሬ ሰብል ሲሰበስብ እና ከበስተጀርባው በርቀት የሚታየው ጭስ በአካባቢው እየተደረገ ያለውን ኃይለኛ ጦርነት ያሳያ፤ በዲኒፕሮፔትሮቭስክ፣ ዩክሬን እአአ ሐምሌ 4/2022

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ዛሬ ኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ገብተዋል።

ፑቲን በቆይታቸው ከዩክሬን መውጫ ያጣው እህል እንዲወጣ አገራቸው የጥቁር ባህርን ልትከፍት በምትችልበት ሁኔታ በሚደረገው ስምምነት ዙሪያ ከቱርክ ፕሬዚዳንት ራሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ጋር ተገናኝተው የሚመከሩ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ በድርድሩ ዙሪያ በሩሲያ፣ በዩክሬን፣ በቱርክና በተባበሩት መንግሥታት መካከል መጠነኛ መሻሻል መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

“ይሁን እንጂ አሁን ባለበት ደረጃ የሚገለጽ ምንም ነገር የለም” ያሉት ቃል አቀባዩ “ አስፈላጊ ከሆነ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ወደ ቱርክ ዋና ከተማ ኢስታንቡል እንደሚያቀኑ ተናግረዋል፡፡

ጉቴሬሽ ትናንት ሰኞ ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ጋር በመካሄድ ላይ ስላለው ድርድር መነጋገራቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር ጃኔት ዬለን አገሮች የሩሲያን የዩክሬን ጦርነት በመቃወም ሩሲያ ወደ ውጭ በምትልከው ነዳጅ ዋጋ ላይ ገደብ በመጣል እንዲተባበሩ አሳስበዋል፡፡

“የኢኮኖሚ ትስስር በሩሲያ ለጦር መሳሪያነት እየዋለ ነው” ያሉት ዬለን” ሩሲያ የዩክሬን ወደቦችን በመዝጋት ዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ እንዲፈጠር ስጋት ሆናለች ብለዋል፡፡

“ኃላፊነት የሚሰማቸው አገሮች ይህን ጦርነት በመቃወም ሙሉ ለሙሉ እንዲያበቃ በአንድነት ተባብረው መስራት ይኖርባቸዋል” ያሉት ሚኒስትሯ “ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች ኃላፊነት የሚሰማቸው አጋሮች፣ በዓለም አቀፉ የኃይል አቅርቦት ገበያዎች ላይ አላስፈላጊ መናጋት በማያስከትል መልኩ ሩሲያ ለምታካሂደው ጦርነት የምታውለውን ገቢ መቀነስ የሚኖርባቸው ለዚያ ነው” ብለዋል፡፡

ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ፣ በሰሚ የምታካሂደው የከባድ መሳሪያ ድብደባ እንዲሁም በሚኮሌቭ የምታደርሰው ፍንዳታና በኦዴሳ የምታደርገውን የሚሳዬል ጥቃት ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የምታካሂደው ጥቃት እንደቀጠለ መሆኑን የዩክሬን ጦር በዛሬው መግለጫው አስታውቋል፡፡

XS
SM
MD
LG