በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፑቲን በማሪዩፖል ድል ማድረጋቸውን አስታወቁ


ፎቶ ፋይል፡- በጦርነት ወቅት የተጎዳው የማሪፖል ቲያትር ቤት ሚያዚያ 4/2022
ፎቶ ፋይል፡- በጦርነት ወቅት የተጎዳው የማሪፖል ቲያትር ቤት ሚያዚያ 4/2022

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ለሁለት ወራት ውጊያ በኋላ ተከባ የቆየችው የማሪዩፖል ከተማ “ነጻ መውጣቷን” አስታወቁ፡፡ የሩሲያ ኃይሎች በአዞቭስታል የብረት ፋብሪካው ውስጥ መሽገው የቀሩትን የዩክሬን ወታደሮችና ሰላማዊ ሰዎች ግን ገና አላስለቀቁም፡፡

ፑቲን ጦራቸው ፋብሪካውን ከመደብደብ ይልቅ “ዝምብ እንኳ እንዳይሾሎክ አድርጎ በመክበብ” እንዲቆይ በትናንትናው እለት ማዘዛቸውም ተመልክቷል፡፡

ይህ ዘዴያቸው ወታደሮቻቸውን ከጥቃት የሚያተርፍ ሲሆን በከበባው የታገቱትን ወታደሮችና ሰላማዊ ሰዎችን ደግሞ በረሀብ የሚቀጣ መሆኑን ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡

የዩክሬን ባለሥልጣናት ከማሪዩፖል ወጣ ብሎ የጅምላ መቃብር ስለመገኘቱ ማስረጃዎች እየወጡ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ማክዛር ቴክኖሎጂ ከተባለው የዩናይትድ ስቴትስ የምስል ድርጅት የወጡ ፎቶግራፎች ቢያንስ 200 የሚሆኑ የጅምላ መቃብሮች ማኑሽ በተባለችው ከተማ ውስጥ መታየታቸውን አመልክቷል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ትናንት ሀሙስ ለዓለም ባንክ እንደተናገሩ አገራቸው በወር 7 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚያስፈልጋት ሲሆን ከሩሲያ ወረራ ጉዳት ለማገገም በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳን ጆ ባይደን ትናንት ሀሙስ መንግስታቸው የ800 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ ለዩክሬን እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

እርዳታው ከሩሲያ ኃይሎች ጋር በምስራቅ ዩክሬን በመካሄድ ላይ በሚገኘው ወሳኝ ውጊያ የኪየቭ ኃይሎችን ያግዛል ተብሎ ተገምቷል፡፡

እርዳታው ከባባድ መድፎችን፣ ሃዊዘርስ የተባሉ በርካታ የረጅም ርቀት መሳሪያዎችን እንዲሁም 144ሺ የሚሆኑ ተተኳሾች መሳሪያዎችና ጥይቶችን” እንደሚያካትት ባይደን ትናንት በዋይት ሀውስ በሰጡት መግለጫቸው አስረድተዋል፡፡

መሳሪያዎቹ በተለይ በዶናባስ ክፍለ ግዛት ዩክሬናውያን ለሚያደርጉት ፍልሚያ ድጋፍ እንዲሆኑ የታሰቡ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን 800ሚሊዮን ዶላሩ የዩናይድ ስቴትስ ምክር ቤት ለዩክሬን ከመደበው ወታደራዊ በጀት አብዛኛውን አሟጦ የመጠቀም ያህል መሆኑን አስታውቀው ምክር ቤቱ ለዩክሬን ኃይሎች ተጨማሪ በጀት እንዲመድብ በቅርቡ የሚጠይቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባይደን ዩናይትድ ስቴትስና ምዕራባውያን አጋሮች 8 ወራት የፈጀውን የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚ ፑቲንን ወረራ የዩክሬን ኃይሎች እንዲመክቱ ለመርዳት ህብረታቸውን አጠንክረው መዝለቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በጸረ ሩሲያ አቋም “በጣም አስፈላጊው ነገር ዓለም አንድ ላይ ማስተባበር ነው” ያሉት ባይደን “እስካሁን ያለው ሁኔታ ጥሩ ነው” ብለዋል፡፡ “ፑቲን መላውን ዩክሬን መቆጣጠሩ አይሳካላቸውም፡፡” ያሉት ባይደን “የፑቲን ዋነኛ እቅዳቸው በጦር ሜዳው ከሽፏል፡፡ ኪየቭ እስካሁን ጸንታ ቆማለች” ብለዋል፡፡

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በተወሰደ እምርጃ የዩክሬን ምጣኔ ሀብትን ለመደገፍና የእየቀጠለ ያለውን የስደተኞች ሰብአዊ እርዳታ ለማለቀላጠፍ የ500 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እየተላከ መሆኑንም ፕሬዚዳን ባይደን አስታውቀዋል፡፡

በአገራቸው ያለውን ጦርነት በመሸሽ የሚወጡ ዩክሬናውያንም ፍላጎታቸው ከሆነ በቶሎ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚመጡበት ሁኔታ የሚያመቻቹ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG