በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“የሰላም አማራጮችን ሁሉ” እንደሚጠቀም ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ


ብልፅግና ፓርቲ
ብልፅግና ፓርቲ

"አሉ የተባሉ የሰላም አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም" የትግራይን ህዝብ ችግሮች ለመፍታት ስምምነት ላይ መደረሱን ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ።

“የትግራይ ህዝብ እየከፈለ ነው” ያለውን “ያልተገባ ዋጋ” ለማስቀረት ጉባዔተኛው መስማማቱን ብልፅግና ፓርቲ የገለፀው ከትናንት /ዓርብ፤ መጋቢት 2/2014 ዓ.ም./ ጀምሮ እያካሄደ ባለው አንደኛ ድርጅታዊ ጉባዔው ላይ ነው።

የጉባዔውን የዛሬ መጋቢት 3 / 2014 ዓ.ም ውሎ በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የፓርቲው የህዝብና የዓለምአቀፍ ግንኙነቶች ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) "የትግራይ ህዝብ ጉዳት የሌላውም ኢትዮጵያዊ ጉዳት ነው" ብለዋል። “በህዝቡ ላይ እየደረሰ ነው” ያሉትን ሰቆቃ ለማስቀረት "አሉ የተባሉ የሰላም አማራጮችን ሁሉ" አሟጦ ለመጠቀም በጉባዔው መወሰኑን ዶ/ር ቢቂላ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ሊወሰዱ ስለሚችሉት “የሰላም አማራጮች” የሰጡት ዝርዝር የለም።

በሌላ በኩል ህወሓት "ትንኮሳና ለዳግም ወረራ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ” የጠቆሙት ዶ/ር ቢቂላ ለዚህም "ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጅት ማድረግና ራስን ማጠናከር ያስፈልጋል" ሲል ጉባዔው መስማማቱንም ገልጸዋል። ብልፅግና ፓርቲ እያካሄደ ባለው አንደኛ ጉባዔው ላይ እስካሁንም መሪው ሆነው የቆዩትን ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ፕሬዚዳንቱ አድርጎ መርጧል። ጉባዔው አቶ ደመቀ መኮንንንና የፓርቲው ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህን ምክትል ፕሬዚዳንቶች አድርጎ ተመርጧቸዋል።

ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ስምምነት ላይ ደርሼበታለሁ ስላለው አቋም ከህወሓት በኩል እስካሁን በይፋ የተሰማ ነገር የለም።

XS
SM
MD
LG