በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፑቲን በምርጫው ለመሳተፍ የድጋፍ ፊርማ አሰባሰቡ


ፎቶ ፋይል፦ የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን
ፎቶ ፋይል፦ የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን

የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የምርጫ ዘመቻ በደጋፊዎቻቸው ፊርማ የተሞሉ 95 ሳጥኖችን ለማዕከላዊ የምርጫ ኮሚሽን አቀረበ፡፡

የሩሲያ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት ፊርማዎቹ ፑቲን እ አ አ በመጭው መጋቢት 17 በሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በዕጩነት መቅረብ የሚችሉ መሆኑን ለማረጋገጥ የተሰጡ ድጋፎች ናቸው፡፡

ፑቲን ምንም እንኳን ከገዥው የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ቢኖራቸውም በምርጫው የሚወዳደሩት ገለልተኛ እጩ ሆነው ነው፡፡

በምርጫው በአሸናፊነት እንደሚወጡ እርግጠኛ ናቸው ለተባሉት ፑቲን ይህ መንገድ ሩሲያን ቢያንስ ለተጨማሪ ስድስት ዓመታት እንዲመሩ ያስችላቸዋል ተብሏል።

የፊርማ ድጋፉን ማሰባሰብ ያስፈለገው የሩስያ የምርጫ ህግ በገለልተኝነት የተመዘገቡ እጩዎች በምርጫው ለመሳተፍ ከ40 የአገሪቱ ክልሎች ቢያንስ 300,000 ፊርማዎችን እንዲያቀርቡ ስለሚያስገድድ ነው፡፡

የ71 ዓመቱ ፑቲን ካሁን ቀደም ሁለት ጊዜ ስልጣናቸውን በመጠቀም ህገ መንግሥቱን እንዲሻሻል በማድረጋቸው በመርህ ደረጃ እስከሰማኒያዎቹ አጋማሽ ዕድሜያቸው ድረስ ስልጣን ላይ መቆየት የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችተዋል፡፡

ፑቲን እ.ኤ.አ. በ1953 ካረፉት የሶቪየት አምባገነን ጆሴፍ ስታሊን በኋላ ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ የቆዩ የክሬምሊን መሪ ናቸው።

እስካሁን ድረስ ለምርጫው ሶስት ተፎካካሪ እጩዎች የቀረቡ ቢሆንም አንዳቸውም ቢሆኑ ፑቲንን የማሸነፍ አቅም የሌላቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ሦስቱ ተፎካካሪዎች የኮሚኒስት ፓርቲ ኒኮላይ ካሪቶኖቭ፣ የሊበራል ዴሞክራት ፓርቲ ሊዮኒድ ስሉትስኪ እና የአዲሱ የህዝቦች ፓርቲ ቭላዲላቭ ዳቫንኮቭ ሲሆኑ ሦስቱም ፓርቲዎች የተባበረች ሩሲያ ፓርቲ አብላጫ ድምጽ በያዘበት ፓርላማ መቀመጫ ያላቸው ናቸው፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG